Thursday, July 11, 2013

ሰባኪ



  
ሰባኪ ምስራቹን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ ሥራ የተጠራ ታላቅ አገልጋይ ነው፡፡ ሥራውም ከስራዎች ሁሉ በላይ ነው፡፡ አገልግሎቱም በምርጫ እና በጸጋ ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ሥራውን ሲሰራም  እግዚአብሄርን ወዶ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሰባኪ ብዙ አድናቂ፣ ተከታይ፣ ክብርና ገንዘብ ፣በሰው ዘንድ መወደድ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ዋና ዓላው ና የነፍሱ ጥማት ኢየሱስ ክርስቶስን መውደድ መሆን አለበት፡፡ በጌታ ፍቅር ውስጥ እስከ ስለሌለ በፍቅር የሚሰራ አገልግሎት ጡረታ የለውም፡፡
    ሰባኪ በእዚአብሔር ፊት ፤-  ሰባኪው በድካሙ ውስጥ የሚቆጠርለት ዋጋ ከምድር አይደለም፡፡ የትኛውም ክፍያና ክብር የምስክርነትን ደሞዝ የመክፈል አቅም የለውም፡፡ ትንሽ ዓላማ ያላቸው ሰባኪዎች በዳረጎት ሲጣሉ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የሰባኪው ዋጋ በሰማይ ያለ ነው፡፡ከሰው ፊት በመንፈሱ  ጨክኖ ዘወር ማለት አለበት፡፡ ልፋቱም እግዚአብሔር ደስ እንዲለው ብቻ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በሁሉም ቦታ በሁሉም ጊዜ ስላለ በዚህ ዓላማ የተቀረጸ ሰባኪ የሁልጊዜ ትጉህ የሁልጊዜ ሰባኪ ይሆናል፡፡ልፋቱን ሰው ቢያውቅለት ባያውቅለት ስሜት የማይሰጠው መንፈሰ ብርቱ ይሆናል፡፡ የሰውን ፊት እና ሙገሳ ትቶ በአምላኩ ፊት የቆመ ሰባኪ እንዴት ተባረከ ይሆን?
ሰባኪ በሰው ፊት - በፍቅር የሆነ ስብከቱ የሰዎችን ድካም ያገናዘበና መፍትሄ ሰጪ መሆን ይባዋል፡፡ሁል ጊዜ እየራራ መስበክ አለበት፡፡ ሰዎች ሁላችን በጣም ደካማ መሆናችንን በእርግጥ በአምላካችን ፊት ብርቱ የሆነ ማንም እንደሌለ አምኖ መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህም ለሁሉ አዛኝ፣ ሰውን በስንፍናው እያሳቀቀ የማይፈርድበት ይልቁንም ከድካም መውጫውን መንገድ በአግባቡ ማሳየት የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡
   ጥንቃቄው
          ከመጠጥ-  መጠጥ አንድን ሰው ፍጹም የሆነ ነጻነት ይሰጠዋል፡፡የሰከረ ደፍሮ የማይሰራው ኃጢአት የለም፡፡ በጌታ ቃል መጠጥን አብዝቶ በመጠጣት የሚወቀሰው ሰው አብዝቶ የመጠጣቱን ነገር ከመንፈሳዊው ስፍራ በተለይ ከአገልጋይ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ሰባኪው አንድ ብርጭቆ መጠጥ ሲጠቀም ሲመለከት ሰነፉ ጠጪ አስር ብርጭቆ አድርጎ ይቀበለዋል፡፡ ስለዚህ ሰባኪው በሰው ፊት ባለመጠንቀቁ ራሳቸውን የማይገዙ እልፍ ሥጋውያንን ሊያበረታታ ይችላል፡፡
          ብዙ መመገብ፤- ብዙ ለምግብ መጎምጀት የጾምን ዓላማ ይቃወማል፡፡ ለሥጋ የተለየ ነጻነት ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ሰባኪው በማዕድ ፊት ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበረሰቡም  በሰው ፊት መመገብን በጥንቃቄ መያዝ የሚፈልግ ነው፡፡ ርቦት ሳለ አሁን በልቼአለሁ በቃኝ የሚልበት ምክንያት ክብሩን ለመጠበቅ ስለሚፈልግ ነው፡፡ ይሄንን ባህል የተገነዘበው ሰባኪ የተሻለ ጥንቁቅ መሆን ይገባዋል፡፡
          መበደር፣- ከሚያስተምረው ሰው ገንዘብ መበደር የሚሰማውን ሰው ልብ ያላላበታል፡፡ አገልጋዩን ተገልጋዩ ዞሮ ዞሮ በእጄ ነው የሚኖረው እያለው በምን ሞራሉ ሊያስተምረው ይችላል? የስነ ልቦና ምሁራን ተዋሽ፣ ለማኝ፣ ተበዳሪ መሆን የሰውን ክብር ዝቅ ያደርገዋል ብለው ያምናሉ፡፡መጽሐፍም ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጹዕ ነው ይላል፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔርን በረከት የሚያስተምር አገልጋይ ከጌታው እጅ ሲበላ መታየት አለበት፡፡የሰውን እጅ ደጅ መጥናት የለበትም፡፡
          ጾታ፣- በተቃራኒ ጾታ መጥመድ ላለመያዝ መጠንቀቅ አንዱ የሰባኪው ሃላፊነት ነው፡፡ከሚያስተምራቸው ምዕመናን መሃከል በፍቅር የተያዘባት ሴት ብትኖር ስሜቱን በቀላሉ መስረቅ ትችላለች፡፡ ስሜት ደግሞ በሰው ፊት ላይ በቀላሉ ሊነበብ የሚችል ገበና ነው፡፡ ሚዛናዊ እንዳይሆንም ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ከሚያገለግላቸው መሃከል ለሕይወቱ አጋር መምረጥ ባይከለከልም የሌላውን ሰው አእምሮ የራሱ ጉዳይ ብሎ የሚያልፍ ሰነፍ መሆን አይገባውም፡፡
          ባዶ ቃል ኪዳን፤- የማይችለውን ቃል ኪዳን መግባት የለበትም፡፡ እንዲህ አደርግላችኃለሁ ብሎ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ከሳበ በኃላ ባያደርገው ወይም በዚህ ሰዓት ፕሮግራም እንጀምራለን ብሎ እርሱ በቦታው ባይገኝ በሰሚዎቹ ዘንድ እንደ ውሸተኛ ሰው ይቆጠራል፡፡
         ሃይል- የሰባኪው ትልቁ ጉልበት ከመለኮት የሚሰጠው ሃይል ነው፡፡ ዘወትር በጸሎት መራስ አለበት፡፡   ከመስበኩ በፊት በጌታው ፊት መንበርከክ አለበት፡፡ ከራሱ የንግግር ችሎታ ከተማረው የስነ መለኮት ትምህርት  ወይም በአጀንዳው ላይ ከአደራጀው ቆየት ያለ ስብከት ይልቅ በእግዚአብሔር ማመኑ እና እርዳታውን መጠየቁ የበለጠ ሃይል ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡ የሰባኪው ሃይል የአዳማጮቹ ብዛት አይደለም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ፡፡ እርሱ ሳይሆን  እሳቱ እንዲሰብክ መፍቀድ አለበት፡፡በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መንፈሱ እንደመሰከረ፤- መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት እንዲናገር ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ ራዕ 3፤6
          እምነት - ሰባኪው በኢየሱስ ክርስቶስ መዳኑን ማመን አለበት፡፡ እኛ ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት አዳነን ያለውን ቅዱስ ጳውሎስ አዋጅ ያመነ መሆን ይገባዋል፡፡ሮሜ 5፤9 ጻድቅ ሰው እግዚአብሔር ባቆመው የምህረት ኪዳን ማለትም በመስቀል ላይ በተከፈለው ፍጹም ዋጋ እንዲሁ በቸርነቱ በጸጋው መጽደቁን ያምናል፡፡ ለዚህ ነው ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ የተጻፈው፡፡ እንደዳነ እርግጠኛ ያልሆነ ሰባኪ በምኩራብ ወይም በመስጊዶች ውስጥ እንጂ በተቀደሰችው ቤተክርስቲያን ፊት ለስብከት መሾም የለበትም፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ምኩራብና የአህዛብ መስኪዶች ሰው ጥሩ ሰው ስለሆነ ነው የሚጸድቀው እንጂ የተከፈለ ዋጋ የለም ብለው ያምናሉና ነው፡፡ ክርስትና የምስራች ናት ደካሞችን ወደ ምህረቱ የምትጠራ ናት ሰው በሥራው ፍጹም መሆን ስላልቻለ በእግዚአብሄር ቸርነት/ጸጋ/ ወደ መንግስቱ መጠራቱን ለዚህም ንጹህ ደም መከፈሉን የምትናገር ሃይማኖት ናት፡፡ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን ቅድስት የምትባለው፡፡ በውሃ /በጥምቀት/ የታጠበች በደሙ የተቀደሰች የጸደቀች በመሆኗ ነው፡፡የጥንት መዝሙር እንዲህ ይላል
                                የውሃ ግድግዳ የደም መሰረት
                                ይሄው ከዚህ አለ የኢየሱስ ቤት
                                ይሄው ከዚህ አለ የአማኑኤል ቤት
   ደግሞም እምነቱ በሌላ አንጻር ጌታ ይረዳኛል፣ ብቻየን አይደለሁም ለአገልግሎት ለሥራ ስነሳም ይረዳኛል ፣ያሳካልኛል፣ የትኛውም ተራራ በፊቴ ደልዳላ ሜዳ ይሆናል ብሎ ማመን አለበት፡፡ ያለእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና፡፡ ዕብ 11፡6 ይቀጥላል
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

No comments:

Post a Comment