Thursday, March 20, 2014

ፍለጋ ወ ስርቆት /ዘማሪ ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ጥቂት የማይባሉ ወንዶች ትዳርን በሩቁ በመፍራት ተመሳሳይ ናቸው፡፡

ፍለጋ ወ ስርቆት /ዘማሪ ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ጥቂት የማይባሉ ወንዶች ትዳርን በሩቁ በመፍራት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ቶሎ ማመን ይቸግራቸዋል፡፡ ሴቶቹ በአብዛኛው አታላዮችና አስመሳዮች እንደሆኑ ይገምታሉ፡፡ መልካም ሚስት በቀላሉ አትገኝም በማለት ወደ ራሳቸው ሰው ሰራሽ የፍለጋ ዘዴ ይገባሉ፡፡ ፍለጋ ሲወጡ ራሳቸው የፈጠሯትን ሴት እንጂ እግዚአብሄር የሰራትን አይመለከቱም ፡፡ አይኗ ጎላ ጎላ ያለ፣ የእጅና እግር ጣቷ ረጃጅም የሆኑ…… ወዘተ ብለው ይነሳሉ፡፡ በአጋጣሚ ካገኛት አንዲት ሴት ጋር ቀጠሮ ይይዛል፡፡ ባገኛትም ጊዜ ስለራሱ ብዙ ይነግራታል ትዳር እንዳማረው ጥሩ ሴት እንደሚፈልግ በውብ ንግግር ያሳምናታል፡፡ ትዳር ፈላጊዋ ልጅም በዚህ ትማረካለች፡፡ ውስጡን መመርመር ሌላ ነገር ማምጣት ነው ብላ ምታስበው ሴት ትዳር ፈላጊውን መቃወም እድልን እንደመጣል ትቆጥራች፡፡ ሁሉን እሺ ትላለች፡፡ ወንዱም ቅድመ ጋብቻ ሴት የምትጠናበት አንዱና ዋናው ግብረ ስጋ እንደሆነ ያምናል የምትወደው ከሆነ ይህን እንድታደርግ ግድ ይላታል ያሳምናታል፡፡ ይሄዳሉ፡፡ ሲመለሱ ግን ተዘጋግተው ነው፡፡ ተመልሶም አይደውል፡፡ ምነው ሲሉት የእግሯ ጣት አጭር ነው ይላችኃል፡፡ መንገደኛው ከሁለተኛዋ ጋር በአጋጣሚ ይገናኛል፡፡ ተመሳሳይ ንግግሮች ያደርጋሉ አዲሷ ሴት ትዳር ፈላጊውን ታምነዋለች፡፡ በሚፈልገው መንገድ ትሄድለታለች፡፡ ሲመለሱ ዝም ዝም ተባብለው ይመጣሉ፡፡ መልሶም አይደውልላት፡፡ ምነው ሲሉት ከለሯ አልማረከኝም ይላል፡፡ ይህ ሰው በየቀኑ ትዳር እየፈለገ ይውላል የፍለጋው መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለትዳር ብዙ ተናግሮ ያሳመናት ሴት አብራው ስለተኛች ይንቃታል፡፡ ሴቶች ሁሉ እንደዚህ ናቸው ብሎ ይፈርዳል፡፡ ጋብዟትም ከሆነ ገንዘቤን አይታ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ይህን በመሰለ ሁኔታ ከብዙ ሴቶች ጋር ያሳለፈው ወንድ ድንግል ማግባት ይፈልጋል፡፡ ጌታ ካልፈቀደለት ሴቶች ጋር መተኛቱን እንደ መጠናናት ይቆጥራል፡፡ አጥኚው እርሱ ትክክል ነው ተጠኚዎቹ ግን ጋለሞታ ናቸው፡፡ይህ ፈሪሳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስታመነዝር አግኝተናታል ብለው ወደ ጌታ አንዲትን ሴት ባመጡ ጊዜ ብቻዋን ነበረች፡፡ዮሓ 8 ወንዱ አልተከሰሰም፡፡ ድንጋይ ለሴቷ ብቻ ነበር የተዘጋጀው፡፡ ይህም ሰው ስለሴቶች የሚሰጠው አስተያየት አስደንጋጭ ይሆንባችኃል፡፡ ምንም ሴት እንደሌለ በእግዚአብሔር ዓለም ለርሱ የሚመጥን እንደጠፋ አመንዝራ ልቡ የነገረውን ለሌሎች ያካፍላል፡፡ እሳካሁን የቆመው ሚስት አጥቶ እንደሆነ በድፍረት ይናገራል፡፡ እርሱ ግን ክብርና ፍቅር መስጠት የሚችል ልብ አጥቶ ነበር የቆመው፡፡ ማንም ያልነካትን ድንግል ሲፈልግ የራሱ ካልሆኑ ነገር ግን የብዙ ወንዶች ሚስቶች/ወደፊት/ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር እየተኛ ነበር፡፡ ይህ ሰው ከአሰልቺ ፍለጋው በኃላ ቆይቶ የራሱ ሚስት ትኖረዋለች፡፡ ከሚስቱ ጋር እንደ መጀመሪያው መደሰት ይቸግረዋል፡፡ ያሳለፈው ብዙ ልምምድ ከፊቱ ይደቀናል፡፡ እርካታ ቢስ ይሆናል፡፡ ትዳሩን በአንካሳ ልቡ ሊመዝን ይጀምራል፡፡ ምክንያት ፈላጊ ቁጡ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሴቶች ስትባሉ… እያለ ሚስቱ ላይ ይፈላሰፋል፡፡ዓለም በጋለሞታ የተሞላች እንደሆነች ያስባል፡፡ ትዳር ፈላጊ የራሱን ድርሻ ብቻ መፈለግ ይኖርበታል፡፡እግዚአብሄር የሰጠው ሚስቱ እንደሆነች የሚለካበት ብዙ መንፈሳዊ ሚዛኖች እያሉት በሥጋ መንገድ መሄድን ማቆም አለበት፡፡ ሰው የራሱን ቤት የሚፈልገው የሰው ቤት እየከፈተ ንብረቱን እየበረበረ እየሰረቀ አይደለም፡፡ በመዝራት ህግ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል የተባለውን ቃል ማስታወስ አለበት፡፡ መልካም የዘራ መልካም፣ መራር ዘራ መራር ያጭዳል፡፡ የሰው ነካ የራሱ ይነካበታል፡፡ የሰረቀ ይሰረቅበታል፡፡ ያስለቀሰ ብዙ ዘመን ሲያለቅስ ይኖራል፡፡ የረዳ ያገዘ ሲታገዝ ይኖራል፡፡ የታመነ ታማኝ ያገኛል፡፡ገላ 6፤7 ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል ቃሉን በመጠበቅ ነው፡፡ መዝ19፤9

1 comment:

  1. ሰው የራሱን ቤት የሚፈልገው የሰው ቤት እየከፈተ ንብረቱን እየበረበረ እየሰረቀ አይደለም፡፡ well said.......

    ReplyDelete