Monday, November 25, 2013

አይናማ ፍቅር- ክፍል አራት /ቀሲስ አሸናፊ/ ይህ ፍቅር እንከን አልባ ፍጹም ነው እያልን አይደለም፡፡ ቀደም ብሎ የተገለጸው መልከም መገለጫ ቢኖረውም አንዳንዴ



አይናማ ፍቅር- ክፍል አራት /ቀሲስ አሸናፊ/
ይህ ፍቅር እንከን አልባ ፍጹም ነው እያልን አይደለም፡፡ ቀደም ብሎ የተገለጸው መልከም መገለጫ ቢኖረውም አንዳንዴ ያኮርፋል፡፡ ፍቅር ነጭናጫ የማድረግ ጸባይ ስላለው ኩርፊያና ያልተጋነነ ጠብ አያጣውም፡፡ ፍቅር ራስን ከመውደድ ስለሚጀምር የራስ ጉዳይ በመሃል መግባቱ አይቀርም በመሆኑም አልተከበርኩም ፣ተረሳሁ፣ ቅድሚያ አልተሰጠኝም፣ እንክብካቤ ጎደልብኝ፣ በማለት መነጫነጩ በነገሮች መፈተኑ አይቀርም፡፡ ከውጭ የሚመጣ ፈተና እና በውስጥ የሚፈጠር ፈተና በግራና በቀኝ ይከተለዋል፡፡
1-
ከውጭ የሚመጣው ፈተና
- ቤተሰብ ምርጫን ሳይቀበል ሲቀር፤- በኑሮ ደረጃ መመዘን፣በዘር ምርጫ ለመደሰት፣በህሊና የሳሉት ሰው አለመሆን
- በሆነው ባልሆነው ጣልቃ በሚገቡ ባልንጀሮች የስነልቦና ጫና
- በስራ ምክንያት ርቆ ተሰዶ በመውጣት የሚፈጠር ልክ የሌለው ናፍቆት እና ብቸኝነት የሚፈጥረው ጫና እና ተስፋ መቁረጥ
2-
ከውስጥ የሚፈጠር፤--
- ባደገበት ማህበረሰብ አኗኗር የተቀረጸው አስተሳሰቡ ሁሉን ተጠራጣሪ አድርጎት ይሆናል፡፡ ስለዚህም ፍቅሩን እውነተኛ አድርጎ ለመቀበል መቸገር፡፡
- ችኩልነቱ ፣የማይረካ ማንነቱ፣ በዓለም ሳለ የነበረው ሜዳ አደግ ልምምዱ/ስለሴቶች ወይም ወንዶች የለመደው ንቀትና ስንፍና የተሞላ ግምቱ/ በእውተኛ ፍቅር እንዳይቆም ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ እነዚህ በአይናማ ፍቅር ውስጥ ሊኖሩ ከሚችሉ እንከኖች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አይናማ ፍቅር መጣላቱ ባይቀርም መጎዳዳት የሚባል ጎጂ ውጤት የለውም፡፡ ይቅርታን በማወቅ እርሱን የሚስተካከለው የለም፡፡ ይቅር ሲል እንደተዋረደ አድርጎ አይቆጥርም፡፡ ይቅርታና ለፍቅር መዋረድ ለፍቅረኛ የሚሰጥ ውብ ስጦታ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ አይናማ ፍቅር ዋጋ መክፈል ይችላል!! ይቅር ሲል፣ ሲያካፍል፣ ሲታገስ፣ ሲለማመጥ፣ ራሱን ረስቶ ነው፡፡ በዓለማውያን አመለካከት እጅግ ሞኝነት በሚባለው መንገድ ሲሄድ የእሳቀ ደስ እያለው ነው፡፡ ለፍቅሩ በከፈለው ዋጋ መልካም የህይወት ፍሬን ለጎጆው ያከማቻል፡፡
ብዙ ሰዎች ኩራትን ከፍቅር ጋር አብረው ገምደው ወገባቸውን ያስራሉ፡፡ እነዚህ የማይስማሙ ክሮች የፍቅርን ሩጫ ውስብስብ የደርጉታል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህን ጹሁፍ የምታነቡ አንዳንድ ሰዎች ፍቅራችሁን በኩራታችሁ ምክንያት አጥታችሁ ልባችሁ እየተናደደ ይሆናል፡፡ ፍቅራችሁን እጃችሁ ውስጥ እንዳታስገቡት ኩራታችሁ በልባችሁ ላይ ይዘልባችኃል፡፡ በዚህ ልባችሁ ትዳር ልትገቡ እንዳትቸኩሉ! በመጀመሪያ መስተካከል ቆንጆ ሆኖ በጌታ ቃል መሰራት የውስጥ ሰውነታችሁን/ልባችሁን/ መንፈሳዊ ቅባት መቀባት ያስፈልጋችኃል፡፡እስቲ ውረዱና ይቅርታን ጠይቁ ደውላችሁ ናፍቆታችሁን ግለጡ ፊታችሁ ይበራል ነፍሳችሁ ታጌጣለች፡፡ጌትነታችሁን ትውት አድርጉና ለፍቅር ባሪያ ሁኑ! እግዚአብሄር የተዋረዱትን ከፍከፍ አድርጓልና፡፡ ማርያም ድንግል ለትሁታን ጸጋን ይሰጣል በልባቸው ሃሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችን በታትኗቸዋል እንዳለች በልባችሁ ኩራት ድንኳናችሁ እንዳይበተን ተጠንቀቁ! ሉቃ 151-52
   አይን አለው የተባለው ፍቅር አለመደሰት መናደድ በስሜት መፈተን ለበት፡፡ የዚህ ፍቅር ልዩ ስጦታው ግን አይኑ ነው፡፡ በችግር ውስጥ ለወደፊት ኑሮው መፍትሄን ይመለከታል፡፡ለምን ተጣላን ፍጹም ሆነን መኖር ነበረብን ብሎ አያብድም! ግን በዛ አለመግባባት የተሸለ መፍትሄ አዘጋጅቶ ይቀጥላል፡፡ ፍቅሩ እውነተኛ መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥበት አቅም አለው፡፡ የወደዳት ወይ የወደደችው አብሬህ አልኖርም ብትለው ሃገር ይያዝ ብሎ ግርግር አይፈጥርም፡፡ ያለ አንተ መኖር ስለማልችል እሰቀላለው በረኪና እጠጣለሁ በማለት ሞኝ አይሆንም፡፡ ይህ ሰው አያፈቅርም እያልኩ አይደለም አያብድም አይታወርም እንጂ! የጌታየ ምርጫ እንጂ የእኔ ውድ ይሁን ብሎ አያለቅስም፡፡ ፍቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን ብሎ ያምናል፡፡ማቴ 6;10
    አንዳንዴ ጫፍ ላይ ያለ ሊፈርስ የደረሰ ይመስላል፡፡ ግን እንደ አልዓዛር ከመቃብር ህያው ሆኖ ይወጣል፡፡ ዮሓ 11;45 በዚህ ውሳኔ ውስጥ አፍቃሪዎቹ የራሳቸው ጥረት ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ችግር ፈጥረው ግንኙነታቸው ይበላሻል፡፡ ያንን ለማስተካከል በራሳቸው አይጥሩም ይልቁን ሁልጊዜ እየጸለዩ ቤታቸውን ዘግተው መፍትሄ ይፈልጋሉ፡፡ እነሱ ኮርተው አኩርፈው የልባቸውን ፍቅር ለእግዚአብሄር ይናገራሉ፡፡ ተፈቃሪው ፍቅር ርቦት አፍቃሪው በሩን ዘግቶ ለአምላኩ ፍቅር እንደያዘው በጸሎት ያጉተመትማል፡፡ የጌታ መልስ ግን ሂጂና ባልሽን ጠርተሸ ነይ የሚል ይሆናል፡፡ አፍቃሪን ሄዶ ማምጣት እንጂ እግዚአብሄር ተሸክሞት እንዲመጣ መጠበቅ እጅግ ሞኝነት ነው፡፡
   አንዳንዶች ደግሞ ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት ስለማይፈልጉ /በተለይ ሴቶቹ/ ለአገኙት ሰው ማካፈል ይቀናቸዋል፡፡ ምንአልባት እድለኛ ከሆኑ መልካም የሚመክር ችግር የሚፈታ ያገኙ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ወንዱ ቂም ይዞ ከፍቶት ነው የሚታረቀው፡፡ ሚስጥሬን አወጣችብኝ የሚል የልብ ኩርፊያ ይሸከማል፡፡ በጣም ቅር ይለዋል፡፡ ኧረ አንዳንዶች አስታራቂ አይጠፋም ብለው ጠብን የሚደፍሩ አሉ! በእነዚህ ሁኔታዎች የሚፈተነው አይናማው ፍቅር በዚህ ወጀብ ውስጥ እየበሰለ ይመጣል፡፡
   ፍቅር ጠብ ጠብ ይላል እንዴ ያለኝን የአንድ ወዳጄን ጥያቄ አልረሳውም፡፡ አዎ! ታራቂውም ፍቅር ገሩም ፍቅር ጠብን ለፍቅር ማረጋገጫ ሲጠቀምበት ማየት የተለመደ ነው፡፡ግን የሚደገፍ ልምምድ አይደለም፡፡
በዚህ ፍቅር ውስጥ አልፎ አልፎ ወቀሳና አሽሙር ተደባልቀው ይገኛሉ፡፡ አፍቃሪው ስሜቱን በቀጥታ መናገርን እንደመዋረድ ስለሚቆጥረው በጎን መናገር ይጀምራል፡፡ አዳማጩም ሰው ስሜቱን መናገር ስለማይችል ነው እንደዚህ ያለኝ የወቀሰኝ ብሎ አይረዳውም፡፡ ሴቷም ስለማይወደኝ ወንዱም ስለማታከብረኝ ነው ብለው አሉታዊ ትርጉም ሰጥተው ይበሳጫሉ፡፡/በዚህ ጉዳይ በቀጣይ በዝርዝር እናየዋለን/ ፡፡ስለዚህ ግልጽ መሆን ቀጥተኛ መሆን/በተለይ ለሴቶች/ የበለጠ ያማረ ዘመን ለማሳለፍ ይረዳል፡፡ይቆየን
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

No comments:

Post a Comment