Monday, March 31, 2014

ሰላም ለሁላችሁ፤- እስቲ ተናገሩ፡-

ሰላም ለሁላችሁ፤- እስቲ ተናገሩ፡- እናት አባት ሳይኖራችሁ ሰው ከወላጅ ሊቀበለው የሚገባውን ፍቅር ተርባችሁ ስታድጉ ወላጅ ሆኖ እየሞላ ሳያጎድል ያሳደጋችሁ እግዚአብሔር አይደለም? እስቲ ተናገሩ፤- መልካም ያላችሁት ሰው ባስቀመጣችሁት ቦታ ሳይገኝ፣ ሚስጢራችሁን አውቆ ሲሳለቅባችሁ ልባችሁ ተሰብሮ ሳለ መንፈስ ቅዱስ ደርሶ ትናትን አላስረሳችሁም? ኑሮዬን ከርሱ/ሷ ጋር አድረጋለሁ ብላችሁ ብዙ ዋጋ የከፈላችሁበት ትዳርና ጓደኝነት ገደል ገብቶ በራችሁን ዘግታችሁ ስታለቅሱ መጥቶ እንባችሁን ያበሰ ጌታ አልነበረም? እስቲ ተናገሩ፤- ሞት ከደጃችሁ የቀረበ እስኪመስላችሁ በብርቱ ታማችሁ በራሳችሁ ተስፋ ቆርጣችሁ ሳለ ቆማችሁ እንድትሔዱ የሆናችሁት በአምላካችሁ እጅ አይደለምን? ውስጣችሁ ከተቀበረ አሳዛኝ ታሪካችሁ ጋር የተቀበላችሁ ጌታ ኢየሱስ አይደለምን?ማቴ 11፤28 ተለወጠ ስትሉት ሳይለወጥ ተወኝ ስትሉት ሳይተው ተቆጣ ስሉት ወዶ… ያሳደራችሁ መልካም አሳዳሪ ጌታችሁ አይደለምን ?እስቲ ተናገሩ፡- በእዳ ተይዛችሁ እዳችሁን የከፈላችሁበት፣ ተገፍታችሁ የፈረደላችሁ፣ ዲዳ ናቸው ብለው ሲከሷችሁ የተናገረላችሁ፣ እንዴት እኖራለሁ ብላችሁ ያኖራችሁ እንዴት እለምዳለሁ ብላችሁ ሃገር ያስለመዳችሁ እንደጥላ የሚከተላችሁ እግዚአብሔር አይደለምን…….pls share it ብቸኝነቴን ያስረሳኝ ወላጅ ደጋፊ የሆነኝ ሰላላ ክንዴን ያበረታ እርሱ ብቻ ነው የኔ ጌታ ይፍሰስ እንባዬ ይሙላኝ አንክሮ ፍቅሩ ሲነካኝ ዓለቴን ሰብሮ አለ በልቤ የእርሱ መብራት መልካምነቱን የማይበት ዘማሪ ዳዊት በቀለ ቁ 2 /በቅርብ የሚወጣ ዝማሬ/

Friday, March 28, 2014

battery low- ሃይል አለቀ የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡

battery low- ሃይል አለቀ የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡ ትደክማለች፡፡ ከሃይሏ ከተለያየች battery low ትላለች፡፡በጋለ ፍላጎት እናመልክ ከነበረ መንፈሳችን ሙትት ይልብናል፡፡ መጸለይ አሰልቺ ሥራ ይሆንብናል፡፡ ቃል ወደምንሰማበት ጉባኤ ለመሄድ ፍላጎት ስለምናጣ አገልግሎቱን እንተቻለን፡፡ ምን እነሱ ሰዓት አያሳጥሩ! የሚሰብኩት በግዕዝ ነው አይገባ! ወ.ዘ.ተ. ቅያሜ ለበስ ንግግሮች እናበዛለን፡፡ ይሄኔ ነፍሳችን battery low እያለችን ነው፡፡ ጓደኞቻችን ስለፓለቲካ፣ ስለኳስ ፣ ስለጌጣጌጥ የሚያወሩ ብቻ ቢሆን ደስ ካለን፣ መንፈሳዊ ሃሳብ ካላቸው ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ ከወደድን ሃይላችን እያለቀ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ያነበብናቸው መጽሐፍት ፍልስፍናና ልብወለድ ብቻ ከሆነ ብዙ ጊዜያችንን ሙዚቃ በማዳመጥ ካሳለፍን ድሮ የነበረን የሞቀ ልባችን ከቀዘቀዘ battery low እያለን ነው፡፡ ወንጌልን በመረዳት ስም ከተግባራዊ አምልኮ ማለትም ለብርቱ ጾም፣ ከጸሎት፣ ድሆችን ከመጎብኘት፣የተቀቡትን ከማክበር ፣ ንስሃ ገብቶ በራስ ስንፍና ከመጸጸት ይልቅ በቃል መደባደብን ከመረጥን ቀይ መብራት እያበራን ነው፡፡ ሌሊት ተነስቶ ማስቀደስን ከተውን፣ ለራሳችን ልዩ ጊዜ ካጣን፣ ከንስሃ አባቶቻችን ጋር የመገናኘት ፍላጎታችን ከሞተብን ነፍሳችን ባትሪ እየጨረሰች እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ወርቃማ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ህይወት ትኩር ብሎ መመልከት ካቃተን፣ ስዕሉ ከህሊናችን ከጠፋ ይህ በመሆኑም ምንም ካልመሰለን ወደ ራሳችን ማየት እንዳለብን ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ሁሌ ትችትና ንቀት የተሞላ ሃሳብ ከልባችን ከወጣ ልባችን ታውቃለህ፣ ትበልጣለህ፣ ሌሎች ግን አይረቡም፣ አያውቁም፣ አልተረዱም ካለን battery low እያለን ነው፡፡የዓሳ አጥማጁን የጴጥሮስን የዋህ ልብ ጥለን የመጽሐፍት ሸምዳጁን የቀያፋን ልብ በውስጣችን ካገኘን አደጋ ላይ ነን፡፡ መቅረዙ የተወሰደበት መብራቱ የጠፋበት ሰው ሆኖ መኖር ምቾት ይሰጣል? በሞተ ህሊና በደነዘዘ ልብ መመላለስ ያስደስታል? የድንኳናችን/ሰውነታችን/ መብራት ጠፍቶ እስከመቼ ይኖራል? እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅክ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ስራህን አድርግ፡፡አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡ ራዕ 2፤5

Thursday, March 20, 2014

ፍለጋ ወ ስርቆት /ዘማሪ ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ጥቂት የማይባሉ ወንዶች ትዳርን በሩቁ በመፍራት ተመሳሳይ ናቸው፡፡

ፍለጋ ወ ስርቆት /ዘማሪ ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ጥቂት የማይባሉ ወንዶች ትዳርን በሩቁ በመፍራት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ቶሎ ማመን ይቸግራቸዋል፡፡ ሴቶቹ በአብዛኛው አታላዮችና አስመሳዮች እንደሆኑ ይገምታሉ፡፡ መልካም ሚስት በቀላሉ አትገኝም በማለት ወደ ራሳቸው ሰው ሰራሽ የፍለጋ ዘዴ ይገባሉ፡፡ ፍለጋ ሲወጡ ራሳቸው የፈጠሯትን ሴት እንጂ እግዚአብሄር የሰራትን አይመለከቱም ፡፡ አይኗ ጎላ ጎላ ያለ፣ የእጅና እግር ጣቷ ረጃጅም የሆኑ…… ወዘተ ብለው ይነሳሉ፡፡ በአጋጣሚ ካገኛት አንዲት ሴት ጋር ቀጠሮ ይይዛል፡፡ ባገኛትም ጊዜ ስለራሱ ብዙ ይነግራታል ትዳር እንዳማረው ጥሩ ሴት እንደሚፈልግ በውብ ንግግር ያሳምናታል፡፡ ትዳር ፈላጊዋ ልጅም በዚህ ትማረካለች፡፡ ውስጡን መመርመር ሌላ ነገር ማምጣት ነው ብላ ምታስበው ሴት ትዳር ፈላጊውን መቃወም እድልን እንደመጣል ትቆጥራች፡፡ ሁሉን እሺ ትላለች፡፡ ወንዱም ቅድመ ጋብቻ ሴት የምትጠናበት አንዱና ዋናው ግብረ ስጋ እንደሆነ ያምናል የምትወደው ከሆነ ይህን እንድታደርግ ግድ ይላታል ያሳምናታል፡፡ ይሄዳሉ፡፡ ሲመለሱ ግን ተዘጋግተው ነው፡፡ ተመልሶም አይደውል፡፡ ምነው ሲሉት የእግሯ ጣት አጭር ነው ይላችኃል፡፡ መንገደኛው ከሁለተኛዋ ጋር በአጋጣሚ ይገናኛል፡፡ ተመሳሳይ ንግግሮች ያደርጋሉ አዲሷ ሴት ትዳር ፈላጊውን ታምነዋለች፡፡ በሚፈልገው መንገድ ትሄድለታለች፡፡ ሲመለሱ ዝም ዝም ተባብለው ይመጣሉ፡፡ መልሶም አይደውልላት፡፡ ምነው ሲሉት ከለሯ አልማረከኝም ይላል፡፡ ይህ ሰው በየቀኑ ትዳር እየፈለገ ይውላል የፍለጋው መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለትዳር ብዙ ተናግሮ ያሳመናት ሴት አብራው ስለተኛች ይንቃታል፡፡ ሴቶች ሁሉ እንደዚህ ናቸው ብሎ ይፈርዳል፡፡ ጋብዟትም ከሆነ ገንዘቤን አይታ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ይህን በመሰለ ሁኔታ ከብዙ ሴቶች ጋር ያሳለፈው ወንድ ድንግል ማግባት ይፈልጋል፡፡ ጌታ ካልፈቀደለት ሴቶች ጋር መተኛቱን እንደ መጠናናት ይቆጥራል፡፡ አጥኚው እርሱ ትክክል ነው ተጠኚዎቹ ግን ጋለሞታ ናቸው፡፡ይህ ፈሪሳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስታመነዝር አግኝተናታል ብለው ወደ ጌታ አንዲትን ሴት ባመጡ ጊዜ ብቻዋን ነበረች፡፡ዮሓ 8 ወንዱ አልተከሰሰም፡፡ ድንጋይ ለሴቷ ብቻ ነበር የተዘጋጀው፡፡ ይህም ሰው ስለሴቶች የሚሰጠው አስተያየት አስደንጋጭ ይሆንባችኃል፡፡ ምንም ሴት እንደሌለ በእግዚአብሔር ዓለም ለርሱ የሚመጥን እንደጠፋ አመንዝራ ልቡ የነገረውን ለሌሎች ያካፍላል፡፡ እሳካሁን የቆመው ሚስት አጥቶ እንደሆነ በድፍረት ይናገራል፡፡ እርሱ ግን ክብርና ፍቅር መስጠት የሚችል ልብ አጥቶ ነበር የቆመው፡፡ ማንም ያልነካትን ድንግል ሲፈልግ የራሱ ካልሆኑ ነገር ግን የብዙ ወንዶች ሚስቶች/ወደፊት/ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር እየተኛ ነበር፡፡ ይህ ሰው ከአሰልቺ ፍለጋው በኃላ ቆይቶ የራሱ ሚስት ትኖረዋለች፡፡ ከሚስቱ ጋር እንደ መጀመሪያው መደሰት ይቸግረዋል፡፡ ያሳለፈው ብዙ ልምምድ ከፊቱ ይደቀናል፡፡ እርካታ ቢስ ይሆናል፡፡ ትዳሩን በአንካሳ ልቡ ሊመዝን ይጀምራል፡፡ ምክንያት ፈላጊ ቁጡ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሴቶች ስትባሉ… እያለ ሚስቱ ላይ ይፈላሰፋል፡፡ዓለም በጋለሞታ የተሞላች እንደሆነች ያስባል፡፡ ትዳር ፈላጊ የራሱን ድርሻ ብቻ መፈለግ ይኖርበታል፡፡እግዚአብሄር የሰጠው ሚስቱ እንደሆነች የሚለካበት ብዙ መንፈሳዊ ሚዛኖች እያሉት በሥጋ መንገድ መሄድን ማቆም አለበት፡፡ ሰው የራሱን ቤት የሚፈልገው የሰው ቤት እየከፈተ ንብረቱን እየበረበረ እየሰረቀ አይደለም፡፡ በመዝራት ህግ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል የተባለውን ቃል ማስታወስ አለበት፡፡ መልካም የዘራ መልካም፣ መራር ዘራ መራር ያጭዳል፡፡ የሰው ነካ የራሱ ይነካበታል፡፡ የሰረቀ ይሰረቅበታል፡፡ ያስለቀሰ ብዙ ዘመን ሲያለቅስ ይኖራል፡፡ የረዳ ያገዘ ሲታገዝ ይኖራል፡፡ የታመነ ታማኝ ያገኛል፡፡ገላ 6፤7 ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል ቃሉን በመጠበቅ ነው፡፡ መዝ19፤9