Monday, July 29, 2013

እብዱ ፍቅር /ክፍል ሁለት/


   
   እብዱ ፍቅር ችኩል ነው፡፡ ዛሬ ያየችውን ሰው ከሶስት ወር ኋላ ለማግባት አይኗን አታሽም፡፡በውጭ ሀገር በማህበራዊ ድህረ ገጽ ያገኛትን ሴት ውጭ ስላለች ብቻ ሳያውቃት ሚስት ለማድረግ ይወስናል፡፡ ቪዛ ካለው በጥቂት ወራት ትውውቅ ወደ ሰርግ እቅድ ለመግባት ትጨክናለች፡፡ ትንሽ ለማወቅ ለመመርመር ፋታ አይሰጥም፡፡ በዚህ ፍቅር የሰከሩ ካላወቁበት በሕይወታቸው ትልቅ ስህተት ለመፈጸም የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ በዚህ እብድ ፍቅር ልባቸው ቆስሎ ጤነኛውን ፍቅር የሚጠሉ፣ ሴቶች ሁሉ እንደዚህ ናቸው ወንዶች ሁሉ እንዲህ ናቸው በማለት ሰውን በክፉ ፈርጀው ብቸኛ መሆንን የሚመርጡ፣ ሰው በቃኝ ብለው የስነልቦና ችግር ሰለባሆኑም ብዙ ናቸው፡፡
     እብዱ ፍቅር ከላይ እንዳየነው ራሱን ብቻ ይወዳል፡፡ ውሳኔው ቸርነቱ ቁጣው ከራሱ ስሜት ብቻ ይነሳል፡፡ ይሄ ፍቅር የማይቆጣጠረው ሰው የለም፡፡ ማንም ከዚህ ብርቱ ማዕበል የሚያመልጥለም፡፡ የስበት ህግ ሰውን ሁሉ እንደሚቆጣጠር ሁሉ ይሄም ፍቅር ሁሉን ይገዛል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት ብሏል፡፡ መኃ መኃ 86  ሞት ያልገዛው ያላሸነፈው ሰው እንደሌለ ሁሉ ይሄም እንዲሁ አድርጓል፡፡ ለዚህ ስሜታዊ ፍቅር ሁሉም የተገዛ ቢሆንም በተለይ አብዝተው ሙዚቃ በሚሰሙ በትዳራቸው ደስታና እርካታ ያጡ፣ልብ ወለድ መጽሐፍት የሚያነቡ፣ የስነልቦና ችግር ሰለባ የሆኑ፣ ወደ ጉርምስና ዕድሜ የገቡ በህልም ለም መኖር የሚወዱ በበለጠ ተጠቂ ይሆናሉ፡፡
   ይሄ ፍቅር እድሜው አጭር ነው፡፡ቢበዛ ሁለት ዓመት! ይህም የአምላክ ጥበብ ይመስለኛል፡፡ ካላንቺ ውሃ አይጠጣልኝም ካላንተ መዋል ማደር አልችልም እየተባባሉ እድሜ ዘመንን በስቃይ መኖር የሚፈልግ ማነው? እንዳልበሰለ ሽሮ በድስት ውስጥ የሚጨፍር፣ ግንፍል ግንፍል የሚል፣ ከተከፈተ ኋላ በረድ የሚል ሆኖ ተሰርቷል፡፡ አንዳንዴ የዚህን ፍቅር መስከን የማይፈልጉ ሰዎች ይገጥማሉ፡፡ እንደግል አስተያየቴ በዚህ እብድ ፍቅር ተይዞ ትዳር ባይገባ እመክራለሁ፡፡ ባለፈው እንዳልነው እውር ነዋ! ጉድለትን ተመልክቶ ራሱን አላዘጋጀም፣ ይበርዳል ይሰክናልብሎ አይጠበቅም፡፡ እቆየ ሲመጣ መስከን ሲጀምር ስግብግቡ ስሜት እየጠፋ ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ አንተ እኮ ድሮ እኔን ሳታይ ምግብ አትበላም ነበር፣ አንቺ እኮ በቀን አስራ ሶስቴ ሳትደውይ አትውይም ነበር ዛሬ ግን በቀን አራት አደረግሽው ጠልተሸኛል ማለት ነው ብለው መወቃቀስ ይጀምራሉ፡፡ ፍቅራችን ድሮ ቀረ ብለው ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ለዚህ ነው ሳይበርድ ሳይሰክን መጋባት የለበትም ያልነው፡፡
    ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው አንዳንድ ወንደ ላጤዎች ለምን አታገቡም ሲባሉ ፍቅር አልያዘኝም ሲሉ መስማታችን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በልጅነታቸው በእብድ ፍቅር ተይዘው ስቃዩን አይተውታልና ዛሬም በዛው ሃይለኛ አውሎ ነፋስ መመታት እና ማግባት ያምራቸዋል፡፡ ያሉበትን የእድሜ ደረጃ ማገናዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ምናልባት ወንደ ላጤው ዛሬ ሥራ የሚበዛበት ይሆንና እንኳን ስለፍቅር ስለኑሮ የሚያስብበት ፋታ የለው ይሆናል፡፡ ምናልባት ዛሬ ሰው በእድሜው ሰክኖ ክፉና ደጉን ለይቶ ማወቅ ስለጀመረ ላገኘው ውበት ሁሉ በቀላሉ እጁን የማይሰጥ ሆኖ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለጋብቻ አስፈላጊው ፍቅር የሰከነው የተረጋጋው እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እድለኛ ሰው ያገባውን ያፈቅራልና፡፡
       ይሄ ስሜታዊ ፍቅር ሙሉ ለሙሉ አጥፊና ጎጂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰራው ሁሉ መልካም መሆኑን እናምናለን፡፡ ዘፍ125 አያያዙን ግን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ፍቅር ይዞት አንቺ የዘለዓለሜ ነሽ ብሎ ምሎ ካሳመናት በ አባት የሌለው ልጅ እናት ያደረጋት ሴት፣ ወይም ንጽህናውን ድንግልናው ክህነቱን ጠብቆ ታምኖ ያደረው፡ በዚህ ፍቅር ተይዞ እንደ ሶምሶን ከደሊ ጋር የተኛ ክብሩን ሜዳ ላይ ጥሎ የዘላለም ጸጸት ተሸክሞ በቤቱ የተቀመጠው ልጅ፣ በስሜት ፍቅር ተሸንፈው ቤተሰቦቻቸውን ተጣልተው ቤታቸውን ለቀው ደግሞም ተከዳድተው ወጥተው የቀሩ ወጣቶች፣ የሚወዱትን ትዳር እና ልጆቻቸውን ትተው ወደ አዲስ ቤት የገቡ፣ የፈቱ አባወራዎች የዚህ ስሜታዊ ፍቅር አሉታዊ ገጽታ ማሳያ ነው፡፡Bottom of Form  Top of Formበዚህ ፍቅር የተያዙ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፍቅሩን ጠባይ ተረድተው ልባቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ስሜታዊ ፍቅር
1- ሁሉን ሜዳ አድርጎ ያሳያል፤- ያፈቀሩትን ሰው ሁሉ እንከን አልባ አድርጎ መመልከት፣ ጉዞውንም አለመጠራጠር ስለሕይወት ግንዛቤ ማጣት ነው፡፡ እንደዚህ የሚሰማው ሰው ስሜታዊ ፍቅር ስለያዘኝ ነው እንዲህ የማስበው ብሎ ሃላፊነትን መውሰድ አለበት፡፡እንዲህ ሲባል ሁልጊዜ ተጠራጣሪ ሁኑ እያልን አይደለም፡፡
2- ለውሳኔ ያስቸኩላል፡- አብሮ ለመኖር ወይም አልጋ ለመጋራት፣ ሚስጥርን ለመካፈል፣ ልብን  ሙሉ ለሙሉ ለመስጠት በደንብ ተረጋግቶ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ክርስቲያኖች እንደመሆናችን የመንፈሳዊውን ዓለም መስመር ጠብቆ መሄድንም ይጠይቃል፡፡ ወድጄዋለሁ ዓለም ቢያልፍ ግድ የለኝም ብሎ እንደ ህጻን ማሰብ እና መወሰን ከመከራ ለመማር ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡ ምክርን ስማ ተግሳጽን ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ፡፡ ምሳ192
3- ጥንቃቄ የጎደለው የዋህነት ይበዛበታል፡፡ ወንዱ ሴቷን የዘለዓለሜ ነሽ ካላንቺ ሌላ ሰው ማሰብ አልፈልግም ባላት ጊዜ በልቧ በእርግጥ ይሄ ሰው ትክክል ነው ከሁሉ በላይ ይወደኛል ያስብልኛል ብላ እንደ ወረደ ታምናለች፡፡ ካመነችው የፈለገውን ነገር ትሆንለታለች፡፡ አንካሳ የዋህነቷ አንደሚጎዳት የምትገነዘበው ቆይታ ነው፡፡ ከትዳር በፊት አብረሽኝ ካልተኛሽ አትወጂኝም ማለት ነው ባላት ጊዜ ፍቅሯን ለመግለጽ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ውሳኔ ትወስናለች፡፡ ከዛ ኋላ የሚመጣውን መዘዝ ሁሉ ብቻዋን ትሸከማለች፡፡

  ስሜታዊው ፍቅር በራሱ መልካም አይደለም ማለት አይደለም ለዋናው ኑሮ መቀራረቢያ ስሜትን ማካፈያ ራስን ማግኛ ሆኖ የሚከሰትበት ሁኔታም አለ፡፡ ትዳርን በፍቅር የሚጀምሩ ብዙ ሰዎች ተጠቅመውበታል፡፡ ፍቅሩ በአተረጓጎሙ ለጥቅም ወይ ለጉዳት ሊሆን ይችላል፡፡ ጠቢቡ የሆነው ነገር ሁሉ የሚሆን ነው የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው እንዳለ መክ 1፤9 የሆነው ነገር አንድ ነገር አስተምሮን ካለፈ መልካም ነው፡፡ያለፈው ልምምዳችን ለዛሬው ኑሯችን ጥሩ ትምህርት ከሆነ ነገ የተሻለ ይሆንልናል፡፡ ፍቅር ይዟችሁ ልባችሁ የደከመባችሁ ሁሉ ለውሳኔ አትቸኩ፡፡ እግዚአብሔርን በቆይታ አዳምጡ፡፡ አባታችሁ አብርሃምንና እናታችሁ ሣራን ተመልከቱ፡፡ አብርሃም ልጅ ትወልዳለህ ከተባለ ኋላ ቃሉ እስኪፈጸም ብዙ ዘመን አለፈ፡፡ ስለዚህም ሣራ አይ እኔ ስላረጀሁ አንተ ያለወራሽ እንዳትቀር ወደ አጋር ግባና ልጅ ውለድ እኔ አቅፌ ልጄ አደርገዋለሁ ብላ በስሜት ምክር ሰጠች፡፡ የልጅ ፍቅር የጠናበት አብርሃምም ይሄን አደረገ፡፡ ከቆይታ አጋር ሣራን መናቅ ጀመረች፡፡ በሁለቱ ትዳር ውስጥ ብርቱ ጥላ ሆነች በዚህም ደጋጎቹ ሰዎች አጋርን ከቤታቸው አባረሩ……ዘፍ16፤6
     ቸኩሎ መወሰን የተበጠበጠ ኑሮ ውስጥ ይከታል፡፡ ጠባይን ይቀይራል፡፡ ሰውን መጥላትና መሸሽ ያመጣል፡፡ ይስሃቅ/ሳቅ/ እያለ እስማኤልን ወደ ቤት ይጋብዛል፡፡ መልካሚቱ ሣራ እያለች ደረት ገልባጯን አጋርን ወደ ጎጆ ያመጣል፡፡ ከስሜት ብቻ ተነስቶ አንድን ውሳኔ ማጽናት ትክክል አለመሆኑን ተረዳችሁ? በቀረው ጊዜአችሁ ልባችሁን አበርቱ፡፡ስሜታዊ ፍቅር ይዟችሁ የምትሰቃዩ ሁሉ ልባችሁ ቆራጥ እየሆነ ሲመጣ ይተዋችኋል፡፡ እግዚአብሔር በራሳችሁ ሰው ላይ እስኪያሳርፋችሁ ድረስ ታገሱ፡፡ አንድ ሰው የራሳችሁ ለመሆኑ የምታረጋግጡት ፍቅር ስለያዛችሁ አይደለም፡፡ ያፈቀራችሁት ሁሉ ለእናንተ የተዘጋጀ ላይሆን ይችላል፡፡ እንደ ህጻን ልጅ በሰው ገንዘብ አታልቅሱ፡፡ ይሄኔ ሌላውም ሰው እግዚአብሔር ለእናንተ በወሰነው ሰው ላይ እያለቀሰ ይሆናል፡፡ይሄ ደግሞ ንፋስን እንደመከተል ከንቱ ነው፡፡  የወደዳችሁት ሰው ልቡን ከከለከላችሁ ወደራሱ ሰው እየሄደ ይሆናልና የራሳችሁን ሰው በትዕግስት ጠብቁ፡፡አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል ተብሎ ተጽፏል፡፡ ምሳ 15;21
 
                ሼር አድርጉት
Top of Form