Tuesday, May 27, 2014

ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/

ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ህዝብ ተከተሉት ማቴ 8፤1 ይህ ምንባብ ጌታ በተራራ ካስተማረ በኋላ ተራራ መውጣት ያቃታቸውን ብዙ ህዝብ ከተራራው በታች እንዳገኘ ይገልጣል፡፡ የልዕልናና የክብር ከፍታ ባለቤት ነችና ተራራ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ሆኖም አማኞች ሁሉ አንድ ሳይቀሩ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የጸጋውን ሚስጢራት የሚካፈሉ አይደለም፡፡ ከተለያየ ድካማቸው ጋር ዓለም ላይ ከግርጌ እንደተበተኑ አሉ፡፡ ቤተክርስቲያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ልጆቿን ማስተማር ያለባት በቤተክርስቲያን ቅጥር ብቻ ነው የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ሃሳባቸውን አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመረምር አስተሳሰቡ እጅግ ጠበብ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ሐዋርያት ምኩራብ ቁጭ ብለው ወንበር ዘርግተው ሰብከው ሳይሆን ሄደው ወጥተው ፣ ሮጠው ወድቀው ተነስተው ነው፡፡ የባህር ሞገድ እየመታቸው መርከባቸው እየተሰበረ፣ ከአውሬ ጋር እየታገሉ ከሮም እስከ እስፔን ከእስያ እስከ አፍሪካ ተሰደው ነው፡፡በዘመኑ እግር ያላት ቤተክርስቲያን ነበረችና ከሮማውያን ርኩሰትና ከግሪክ ፍልስፍና የእግዚአብሔርን በጎች ነጥቃ ወደ ሰማያዊ ጥሪ አድርሳለች፡፡ ቀድሞም የቤተክርስቲያን ራስ እና አስተዳዳሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ ብሉ አዟል፡፡ሂዱ የሚለው ትዕዛዝ ተቀምጣችሁ ጠብቁ ከሚል ሃሳብ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ማቴ28፤19 ወንጌል መሰበክ ያለበት ወዳጆቼ እንደሚያምኑበት በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት መሆኑ ዋንኛ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ያልመጣውስ? ካለማወቅ የተነሳ ሃይማኖት ዝም ብሎ ማህበራዊ ልማድ ብቻ ነው ብሎ የቆመውስ? በዓለም ወለድ ፍልስፍና ታስሮ የመስቀሉን ቃል ሳይሰማ በሥጋ የሚኖረውስ? በየዋህነቱ ብቻ ኖሮ ለበላተኞች ራት ለመሆን ጫፍ የደረሰው? ይህን ሁሉ ደካማ መንጋ ማነው የሚያተርፈው? ወንጌል ለቆራቢው ስብከት ቤተክርስቲያን ለሚተጋው ምዕመን ብቻ ከሆነ ሸክም የከበደበት ደካማው ዕጣው ምንድነው? ያላመኑስ እንዴት ወንጌል ሊሰሙ ይችላሉ? ስለዚህ ወንጌልን በሁለቱም መንገድ በተደራጀ ሁኔታ ልናዘጋጅላቸው ተገብቷል፡፡ 1- ቤተክርስቲያን መምጣት ለቻሉ፡- ቤተክርስቲያን የመጡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ወንጌላችን ልትረዳቸው ይገባል፡፡ በየክብረ በዓላቱ በወርና በዓመት አባቶቻችን በሰሩት ቅዱስ ስርዓት መሰረት ሰዎች ያለምንም ቀስቃሽ ወደ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ እነዚህ መንጎች በተሰናዳ ወንበር በተረጋጋ መንፈስ እነሱ ባሉበት ደረጃ ህይወታቸውን ከአምላካቸው ጋር ሊያጣብቅ የሚያስችል ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዝናብ ቢመጣ ያለምንም ክፍያ የሚሰበሰቡበት ንጹህ አዳራሽ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምክር አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸው የተለዩ ክፍሎች ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከንስሃ አባቶቻቸው ጋር ሚስጢራቸውን የሚያወሩባቸው ከለል ያሉ ቦታዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕጻናቶቻቸው አማርኛ ወይ ሌላ ሃገር በቀል ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሆኑ እንዲሁም በከተሞች የሚኖሩ ከሆነ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እንዲሁም አዲሱን አማርኛ የሚናገሩ መምህራን እንዲያገኗቸው ልዩ መርሃ ግብር/እንደቦሌ መድሐኒዓለም/ ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከተገኙም አለቆች እና የአውደ ምህረት ገምጋሚዎች እንዲደነቁ ተብሎ ሳይሆን ህዝቡ በሚገባ እንዲገባው እና እንዲመሰረት ማድረግ የሚችል ትምህርት በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት/ጥናት/ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ በቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን አንድ በአንድ ምዕራፍ በምዕራፍ ማስተማር ከጀመርን በጎቹ ከውጭ በሚሰሙት አዲስ ስብከት አይደነቁም፡፡ በቤታችን ሰምተነዋል እናውቀዋለን ብለው ጸንተው ይቆማሉ፡፡እንዲሁም ልዩነትን የሚጸየፉ አንድ አይነት መንፈሳዊነት ያላቸው ያደርጋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን አንድ ዓይነት በማድረግ የተለየ መጽሐፍ ነው፡፡ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ቁንጽል ጥቅስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎቻቸውን አደላድለው እንዲያውቁ ማድረግ እንችላለን፡፡ሌላውን ለመርታትና ለማሳመን ብቻ ሳይሆን ራሳቸው እንዲያምኑ አድርጎ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ 2- ከቤተክርስቲያን ውጪ፤- ከቅጥሩ ውጪ ያለው ህዝብ ብዙ ነው፡፡ በምክንያት የታሰረ፣ አውቃለሁ የሚል፣ በዓለም እና በአጋንንት አሰራር የተያዘ፣ እንዲሁ ተፈጥሮአዊ ሰው የሆነ፣ ያላመነ ያልተጠመቀ…….. እጅግ ብዙ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን አስተምራ አምና የመረቀቻቸው፣ ክህነት ድቁናና ቅስና የሰጠቻቸው፣ በጸጋ እግዚአብሔር ሰባኪ ሆነው የተለዩ ስብከቶቻቸውን የአውደ ምህረት ብቻ አድርገው ሊያዘጋጁ አይገባም፡፡ በለቅሶ ቤት፣ ሰርግ ቤት፣ ምዕመናን ቤት/ቤተሰባዊ ጉባኤ/፣ እንደ ፊሊጶስ /በሰረገላ /መጓጓዣ ውስጥ፣ ሴተኛ አዳሪዎች በሚሰበሰቡባቸው ቤቶቻቸው፣ ሰራተኞች ስራ ፍለጋ በጠዋት በሚኮለኮሉባቸው አደባባዮች፡፡ ሊስትሮ እያስጠረጉ ለሊስትሮዎች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ ለገበሬው በእርሻ ስፍራው በጽዋ ማህበራት፣ በሆስፒታል ይህን በመሰለ ቦታ የመዳን ወንጌል እንዲሰሙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጌታ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር እንደዚህ ነው የሰበከው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሐይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህን ኢየሱስን ተመልከቱ ብሎናል፡፡ዕብ 3፤1 በዚህ መንገድ ካልሰራን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤተክርስቲያን እንደ አውሮፓውያን አብያተክርስቲያናት የአረጋውያን ብቻ መሰብሰቢያ ልትሆን ትችላለች፡፡ መሪዎቿና ልጆቻቸው በቋንቋ እና በመረዳት/understanding/ የማይግባቡ በመካከላቸው ያለው ድልድይ የሰፋ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህን ተልዕኮ እየተቆጣጠረች ልትመራ ይገባታል፡፡ በዚህ መንገድ የስህተት ትምህርታቸውን በማስተማር ከመንጋው ለይተው ሜዳ የሚጥሉ ሰነፎች በዓለም በብዛት አሉና፡፡ በውጭ ያሉትን ካስተማሩ በኋላ ወደ በረቱ ማስገባት ግዴታ ነው፡፡ ሰብዓ ሰገልን የመራው ኮከብ ቤተልሔም አድርሷቸው እንደተሰወረ አገልግሎታችን በጎቹን አምጥቶ ለሞተላቸው ጌታ በቤቱ ማስረከብ አለበት፡፡ማቴ 2፤9 ምክንያቱም ጸጋው የሚገኝባቸው ሚስጢራት ማለትም ጥምቀት ቅዱስ ቁርባን ተክሊል ወ.ዘ.ተ በውጭ የማይፈጸሙ ናቸውና፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከውጭ የሚገቡት ውስጥ ከሚጠብቋቸው ምዕመናን ጋር መንፈሳዊ ህብረት መፍጠር አለባቸውና ነው፡፡ህብረቱ እስከ ጽዮን ተራራ እስከ ሰማይ የሚደርስ ነው፡፡ ይቆየን፡፡ዕብ 12፤22 ጌታ ሆይ ጉልበታችንን አበርታ እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት