Tuesday, September 30, 2014

እንዲሁ መውደድ….. እንዴት የተወደዳችሁ ሆይ አንድ ሰው ጌታውን የሚወደው ለምንድን ነው? ስለረዳው፣ ስላጸደቀው፣ ስለሰማው፣ ስለሚረዳው ወ.ዘ.ተ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁ ስለ መውደዱ ግን አስቦ አያውቅም፡፡ የአንድ አማኝ ልዩ ፍላጎቱ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ነው ወይ መንግስቱን የሚሰጠውን ጌታን መውረስ ነው? እኛና እግዚአብሔር ያለን ግንኙነት በጥቅማችን ላይ ብቻ ከተንጠለጠለ ፍቅራችን ጉዳዩ ላይ አንጂ ሰጪው ላይ አይደለም ማለት ነው፡፡ይሄ ደግሞ እንከን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን የሚወዱት የጸጋን ትምህርት ባልተስተካከለ ሁኔታ ሲሰሙ ነው

እንዲሁ መውደድ….. እንዴት የተወደዳችሁ ሆይ አንድ ሰው ጌታውን የሚወደው ለምንድን ነው? ስለረዳው፣ ስላጸደቀው፣ ስለሰማው፣ ስለሚረዳው ወ.ዘ.ተ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁ ስለ መውደዱ ግን አስቦ አያውቅም፡፡ የአንድ አማኝ ልዩ ፍላጎቱ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ነው ወይ መንግስቱን የሚሰጠውን ጌታን መውረስ ነው? እኛና እግዚአብሔር ያለን ግንኙነት በጥቅማችን ላይ ብቻ ከተንጠለጠለ ፍቅራችን ጉዳዩ ላይ አንጂ ሰጪው ላይ አይደለም ማለት ነው፡፡ይሄ ደግሞ እንከን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን የሚወዱት የጸጋን ትምህርት ባልተስተካከለ ሁኔታ ሲሰሙ ነው፡፡ ለተወሰኑት ጸጋ በኃጢአት ለመኖር ከጌታ ኢየሱስ ፍቃድ የሚቀበሉበት ኪዳን ይመስላቸዋል፡፡ ያለ ኢየሱስ ለኔ ወገን የለኝም የሚሉ ጥቅሶችን፣ ነቆራ አዘል አባባሎችን መጠቀም ይጀምራሉ፡፡ አይናቸውን ጨፍነው መዘመር ምናልባትም ከአይን ዘለላ እንባን ማውጣት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ወደ እግዚአብሔር እንደ ደረሱ ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁል ጊዜ ከስንፍናቸው ጋር፣ ከድፍረታቸው ጋር፣ ከስድባቸው ጋር፣ ከፍርዳቸው ጋር፣ ከንቀታቸው ጋር፣ ከአሽሙራቸው ጋር አሉ፡፡ ጌታን የወደዱት ጸጋ ስላለ ነው እንጂ ሰውን መውደዱ፣ ንጽሕናው፣ ከልብ የዋህነቱ፣ ትህትናው፣ ለሰው ሟች መሆኑ ነክቷቸው አይደለም/ለአንዳንዶቹ/ ፡፡ ምክንያቱም ከጌታ ሕይወት የቅድስና ፍንጣሪ ነክቷቸው አይታይም፡፡ ለነሱ ግን ኢየሱስ ልዩ ነው ከአብም ከመንፈስ ቅዱስም ይበልጣል፡፡እነዚህ ሰዎች ጌታ ኢየሱስን የወደዱት በኃጢአት ከሚወቅሳቸው ህሊናቸው ወቀሳ በነጻ ጸድቃችኋል የተባለው ትምህርት ስላሳረፋቸው ብቻ ነው፡፡ ቅዱሳንን የምንወዳቸው ስለሚያማልዱን በረከታቸው ስለሚደርሰን ብቻ ነውን ? ይሄ ባይሆን ልንወዳቸው እንችላለን? አንዳንድ ሰዎች አከሌ አያማልድም የሚል ትምህርት ሲያሸንፋቸው ከልባቸው ስፍ ስፍ ብለው ይወዱት የነበረውን ቅዱስ ወደ መጥላት ይመጣሉ፡፡ በጆሯቸው ስለዛ ጻድቅ መስማት አይፈልጉም፡፡ ያው ወደዋለሁ አከብረዋለሁ ብለው ከልባቸው ጥላቻ ለመሸሽ በአፋቸው ብቻ ይሞክራሉ፡፡ ግን የእግዚአብሔርን እንቁዎች እንዲሁም ቢሆን ለምን መውደድ አቃታቸው? ቀሪዎቹ አከሌ እንዲህ አድርጎልኛልና እርሱ ለእኔ ይቅርታ አድርጉልኝ እንጂ ከእግዚአብሔር በላይ ሆኖ ይታየኛል ሲሉ ሳያፍሩ ይናገራሉ፡፡ ወንጌል ሰብኮ ለንስሃ ስላበቃቸው ክርስቶስን በኑሮው ማሳየቱ አይነካቸውም ዲቪ በስለት ስላገኙበት ነው የወደዱት፡፡ እነዚህ ሰዎች የሞተውን ቅዱስ እንጂ በሕይወት ያለውን ጻድቅ አይወዱም፡፡ እንደ ያዕቆብ ልጆች ቅዱሱን ይገድላሉ መቃብሩን ያሳምራሉ፡፡ ማቴ 23፤29-30 በሕይወት ቅዱስ የለም ብለው ያምናሉ፡፡ ጻድቅ ድሮ ቀረ ባዮች ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመኑ ለእግዚአብሔር ሃሳብ ያደረውን ቅዱስ ከቤተክርስቲያን እስኪወገድ ድረስ ያሳድዱታል፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ አይሁድ የክስ ዝርዝራቸው አያልቅም፡፡ ዛሬ ያለው የእግዚአብሔር ሰው አይረባም፡፡ እግዚአብሔርን ፈርተው እንጂ የዛሬው እግዚአብሔር ራሱ እንደ ድሮው አይደለም ለማለት ሁሉ ይፈልጋሉ፡፡ የዛሬው ቅዱስ ምዕመን፣ ጳጳስ፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ አስተናባሪ ፣ መካሪ፣ ሰንበት ተማሪ ምንም ረብ የሌለው ተራ ነው፡፡ የሞቱት ግን ስለሚጠቅሟቸው የከበሩ ናቸው፡፡ ባይጠቅሟቸው ግን እነርሱንም አይጠቅሙም ባይ ይሆኑ ነበር፡፡ስለዚህ በስሙ የምታመኑ ሆይ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረው መምህር አባት እንዲሁ መውደድን ልንማር ይገባል፡፡ አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን አንዲሁ ወዷል፡፡ዮሐ3፤16 ተብሎ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔርም ስለጠቀመን ብቻ ሲወደድ ደስ የሚለው አይመስለኝም፡፡ ጻድቁም ስለጠቀመ ብቻ ከተከበረ ደስ የሚለው አይደለም፡፡ ጥቅሙ በረከቱ ዳረጎት ሆኖ ይሰጣል፡፡ በእምነት የሆነ ፍቅር በነጻ የሆነ መውደድ እጅግ ደስ ያሰኛል፡፡ያለ እምነት የሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ሮሜ 14፤23 እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

Wednesday, September 24, 2014

ሰላም ለሁላችሁ፤- መስቀል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል መሰቀሉን የምናስብበት ነው

ሰላም ለሁላችሁ፤- መስቀል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል መሰቀሉን የምናስብበት ነው፡፡ ገላ 3፤13 መሰቀሉ የጌታን አሸናፊነት ያሳየ ነው፡፡ ክርስቶስ ገዳዮችን ብቻ ሳይሆን ሞትን የተዋጋ ነጻ አውጪ ነው፡፡ በመስቀል ሲሞትም እየማረከ ከፍ እያለ ነበር እንጂ እንደ ሰው እያለቀለት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ትግሉን በትንሳኤ ደምድሞታል፡፡ ስለዚህ ሞቱን ክብር ብሎ ጠርቶታል፡፡ ዮሐ 17፤2 መሰቀሉም ወደ ላይ ከፍ ማለቱ ነበር፡፡ ተሰቀለ ከፍ ከፍ አለ ማለት ነው፡፡..እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እሰበስባለሁ..ዮሐ 12፤32 እንዳለ፡፡ እኛም በመሰቀሉ ወደ ላይ ክፍ ብለናል፡፡ ወደ ፊት ወደ እርሱ ለመነጠቅ ከበጉ ሰርግ ለመታደም በተስፋ የምንጠብቅበትን መግባት አግኝተናል፡፡ ምልክቱ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነው … ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ሆኖ ተሹሟል…ሉቃ 2፤35 መስቀሉም በጉ የተሰዋበት ቅዱስ መሰዊያ ነው፡፡ ያዳኛችንን ቅዱስ ሞት የምናስብበት ነው፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ፡፡ እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት www.ashenafigmariam.blogspot.com

Friday, September 19, 2014

ሰላም ለሁላችሁ፤- ምህረቱ ለሚፈሩት እስከ ትውልድ ትውልድ ነው…ሉቃ 1፤50 በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ሆይ፤- እግዚአብሔርን በፍቅር መፍራት ስለእርሱ ከማወቅ ይጀምራል፡፡ ጌታችሁን የምታውቁት ስለርሱ ፍላጎትና ፍለጋ ሲኖራችሁ ነው፡፡ በርግጥ አሁን ያላችሁበት ኑሮ የማንንም እርዳታ የማይፈልግ ይሆናል፡፡ ጊዜአችሁን ምቾታችሁን ሊያስጠብቅላችሁ ይችላል በምትሉት ነገር ብታጠፉ ደስ ይላችኋል፡፡ ነገር ግን እናንተ የዛሬው ሰዎች ብቻ አይደላችሁም የምድርም ኑሮ ብቻ አይደለም ያላችሁ፡፡ትውልዳችሁን የሚረከብ ጌታ አለ፡፡ ዘላለም የሚባል ዓለም አለ፡፡ ወደዛ የምትደርሱበት መንገድ ጌታ ነው ፡፡ ለትውልዳችሁ የምታወርሱት ከምድር የሆነ ጌጠኛ ድንጋይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንደ አብርሃም የዘላለም ምህረት የመለኮት ጥበቃ ለልጆቻችሁ ማቆየት አለባችሁ፡፡ ይህን የምታገኙት ልዑሉን ስታውቁትና ስትፈሩት ነው፡፡ ለትውልዳቸው ርግማን ትተው ያለፉ የትናንት ሰዎች ነበሩ፡፡ የሰው ደም በከንቱ ያፈሰሱ፣ በድሃ እንባ የታጠቡ፣ ሃገር ያፈረሱ፣ ልዑሉን የረገሙ፣ ማምለኪያውን ያቃጠሉ፣ በጉቦ የፈረዱ፣ ባይተዋሩን ፊት የነሱ… እነዚህ መርገምን ለትውልዳቸው ትተው ሄደዋል፡፡ የፈሩት ግን ተመርቀዋል ከነልጆቻቸው ምህረትን ጠግበዋል፡፡የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ምሳ 1፤7 ተባረኩ፡፡ እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት visit www.ashenafigmariam.blogspot.com

Tuesday, July 8, 2014

ሰላም ለሁላችሁ፤- አገልግሎት ፍላጎት ነው ወይስ ቅባት?

ሰላም ለሁላችሁ፤- አገልግሎት ፍላጎት ነው ወይስ ቅባት? ዛሬ ብዙ ሰው መናገር ስለሚቻል ሰባኪ እንደሚኮን ትንሽ የማይሻክር ድምጽ ካለ መዘመር እንደሚቻል የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ አርቲስቱና ዘፋኙ በትርፍ ሰዓቱ ዘማሪ ነው፡፡ በክብረ በዓላት ቀን ደግሞ ቅልጥ ያለ ጨፋሪ ሆኖ ይቆማል፡፡ በትርፍ ሰዓትሽ ምን ያደስትሻል ተብላ አንዲት አርቲስት በቀደም እሁድ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተጠየቀች፡፡ ለስለስ ያለሙዚቃ በተለይ የሚያስጨፍር ከሆነ ምድር አይበቃኝም አለች፡፡ ይህችው ሴት ለቤተክርስቲያን መርጂያ መዝሙር ዘምራ/ ለቤተክርስቲያ ያረገችውን መልካም ስራ ባደንቅም/ በየቤተክርስቲያኑ መድረክ አትጠፋም፡፡ አንዳንዴም ቤተክርስቲያን ተደፈረች ድረሱ የሚል ሃሳብ ወለድ ድራማዎችን እየሰሩ የእነሱ መቅደስ /ሰውነታቸው/ ዓለምን የሚያገለግልና ውሳኔአቸውም ለእግዚአብሔር ያልተሰጠ ሆኖ ይታያል፡፡ አንዱ አርቲስት ቀደም ብሎ ጥሩ የሚባል ዝማሬ ሰራ፡፡ ቆየት ብሎ በአንድ መጽሔት እኔ ዘማሪ መሆን አልፈልግም ቤተክርስቲያንን ለመርዳት ነው! ብሎ ቃለምልልስ ሰጠ፡፡ እግዚአብሔር ጉሮሮ ሳይሆን ልብ ነበር የሚያስፈልው፡፡ የሚቃጠል መስዋት ደስ አያሰኝህም የእግዚአብሔር መስዋት የተሰበረ ልብ ነው፡፡ መዝ50፡17 አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የተቀቡ ለዚህ አገልግሎት ራሳቸውን የሰጡትን ዘማሪያንን አይናችሁ ላፈር ብለው እኒሁ የሁለት ቤት ሰዎችን ልዩ አገልጋያቸው አድርገው ይሰይማሉ፡፡ ማንም ሰው ለጌታው ክብር ሊሰጥ እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አውደ ምህረቱና መቅደሱ እግዚአብሔር በጸጋው ቅባት በለያቸው ሰዎች ነው መገልገል ያለበት፡፡ የእግዚአብሔር የሆነ ልዩ ነገር ከሌለ ቅድስና እንዴት ይለያል? የተነሳ ሁሉ ነፍሱን ለጌታው ብቻ ወስኖ ሳይሰጥ ላገልግል ካለ ዓለማዊነት ሰተት ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ይገባል፡፡ቤተክርስቲያ የምትጠፋበት ዋናው መንገድ ዓለማዊነት መንፈሳዊ ለምድ ለብሶ ሲገባባት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ዘፋኞች በድምጻቸው ብቻ ዘማሪዎች ነበሩና ትንሽ ከፍ ሲሉ የተደቁ ዘፋኞች ወደ መሆን ይቀየራሉ፡፡ እድገቱ ከዘማሪነተት ወደ ዘፋኝነት የሆነ ይመስል ያኔ የሰንበት ተማሪ ዲያቆን ነበርኩ ይሉናል፡፡ ማንም ይህን ሆኖ ከሆነ ዘፋኝ የሆነው እንዲህ ብሎ በመናገሩ ማፈር አለበት፡፡ እግዚአብሔር በቂ እንጀራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ እርሱ የዚህ ዓለም ጥበብ የማይደግፈው ራሱን የቻለ ብልጥግና ነው፡፡ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚመጣው ጌታን ሊያግዝ ሳይሆን ራሱን ሰው አድርጎ ሊሰራ ነው፡፡ ፈርቶ፣ ትሁት ሆኖ፣ ለመናገር ሳይቸኩል ደግሞም በእምነት አድጎ ዓለሙን ርግፍ አድርጎ ሊኖር መሆን አለበት፡፡ አገልግሎትም በቅባት እና በመጠራት እንጂ በታለንት ወይ በችሎታ አይደለም፡፡ በመንፈሴ እንጂ በሐይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ዘካ 4፤6 ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና፡፡ ያዕ 3፤1 እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

Tuesday, May 27, 2014

ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/

ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/ ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ህዝብ ተከተሉት ማቴ 8፤1 ይህ ምንባብ ጌታ በተራራ ካስተማረ በኋላ ተራራ መውጣት ያቃታቸውን ብዙ ህዝብ ከተራራው በታች እንዳገኘ ይገልጣል፡፡ የልዕልናና የክብር ከፍታ ባለቤት ነችና ተራራ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ሆኖም አማኞች ሁሉ አንድ ሳይቀሩ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የጸጋውን ሚስጢራት የሚካፈሉ አይደለም፡፡ ከተለያየ ድካማቸው ጋር ዓለም ላይ ከግርጌ እንደተበተኑ አሉ፡፡ ቤተክርስቲያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ልጆቿን ማስተማር ያለባት በቤተክርስቲያን ቅጥር ብቻ ነው የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ሃሳባቸውን አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመረምር አስተሳሰቡ እጅግ ጠበብ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ሐዋርያት ምኩራብ ቁጭ ብለው ወንበር ዘርግተው ሰብከው ሳይሆን ሄደው ወጥተው ፣ ሮጠው ወድቀው ተነስተው ነው፡፡ የባህር ሞገድ እየመታቸው መርከባቸው እየተሰበረ፣ ከአውሬ ጋር እየታገሉ ከሮም እስከ እስፔን ከእስያ እስከ አፍሪካ ተሰደው ነው፡፡በዘመኑ እግር ያላት ቤተክርስቲያን ነበረችና ከሮማውያን ርኩሰትና ከግሪክ ፍልስፍና የእግዚአብሔርን በጎች ነጥቃ ወደ ሰማያዊ ጥሪ አድርሳለች፡፡ ቀድሞም የቤተክርስቲያን ራስ እና አስተዳዳሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ ብሉ አዟል፡፡ሂዱ የሚለው ትዕዛዝ ተቀምጣችሁ ጠብቁ ከሚል ሃሳብ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ማቴ28፤19 ወንጌል መሰበክ ያለበት ወዳጆቼ እንደሚያምኑበት በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት መሆኑ ዋንኛ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ያልመጣውስ? ካለማወቅ የተነሳ ሃይማኖት ዝም ብሎ ማህበራዊ ልማድ ብቻ ነው ብሎ የቆመውስ? በዓለም ወለድ ፍልስፍና ታስሮ የመስቀሉን ቃል ሳይሰማ በሥጋ የሚኖረውስ? በየዋህነቱ ብቻ ኖሮ ለበላተኞች ራት ለመሆን ጫፍ የደረሰው? ይህን ሁሉ ደካማ መንጋ ማነው የሚያተርፈው? ወንጌል ለቆራቢው ስብከት ቤተክርስቲያን ለሚተጋው ምዕመን ብቻ ከሆነ ሸክም የከበደበት ደካማው ዕጣው ምንድነው? ያላመኑስ እንዴት ወንጌል ሊሰሙ ይችላሉ? ስለዚህ ወንጌልን በሁለቱም መንገድ በተደራጀ ሁኔታ ልናዘጋጅላቸው ተገብቷል፡፡ 1- ቤተክርስቲያን መምጣት ለቻሉ፡- ቤተክርስቲያን የመጡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ወንጌላችን ልትረዳቸው ይገባል፡፡ በየክብረ በዓላቱ በወርና በዓመት አባቶቻችን በሰሩት ቅዱስ ስርዓት መሰረት ሰዎች ያለምንም ቀስቃሽ ወደ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ እነዚህ መንጎች በተሰናዳ ወንበር በተረጋጋ መንፈስ እነሱ ባሉበት ደረጃ ህይወታቸውን ከአምላካቸው ጋር ሊያጣብቅ የሚያስችል ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዝናብ ቢመጣ ያለምንም ክፍያ የሚሰበሰቡበት ንጹህ አዳራሽ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምክር አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸው የተለዩ ክፍሎች ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከንስሃ አባቶቻቸው ጋር ሚስጢራቸውን የሚያወሩባቸው ከለል ያሉ ቦታዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕጻናቶቻቸው አማርኛ ወይ ሌላ ሃገር በቀል ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሆኑ እንዲሁም በከተሞች የሚኖሩ ከሆነ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እንዲሁም አዲሱን አማርኛ የሚናገሩ መምህራን እንዲያገኗቸው ልዩ መርሃ ግብር/እንደቦሌ መድሐኒዓለም/ ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከተገኙም አለቆች እና የአውደ ምህረት ገምጋሚዎች እንዲደነቁ ተብሎ ሳይሆን ህዝቡ በሚገባ እንዲገባው እና እንዲመሰረት ማድረግ የሚችል ትምህርት በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት/ጥናት/ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ በቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን አንድ በአንድ ምዕራፍ በምዕራፍ ማስተማር ከጀመርን በጎቹ ከውጭ በሚሰሙት አዲስ ስብከት አይደነቁም፡፡ በቤታችን ሰምተነዋል እናውቀዋለን ብለው ጸንተው ይቆማሉ፡፡እንዲሁም ልዩነትን የሚጸየፉ አንድ አይነት መንፈሳዊነት ያላቸው ያደርጋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን አንድ ዓይነት በማድረግ የተለየ መጽሐፍ ነው፡፡ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ቁንጽል ጥቅስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎቻቸውን አደላድለው እንዲያውቁ ማድረግ እንችላለን፡፡ሌላውን ለመርታትና ለማሳመን ብቻ ሳይሆን ራሳቸው እንዲያምኑ አድርጎ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ 2- ከቤተክርስቲያን ውጪ፤- ከቅጥሩ ውጪ ያለው ህዝብ ብዙ ነው፡፡ በምክንያት የታሰረ፣ አውቃለሁ የሚል፣ በዓለም እና በአጋንንት አሰራር የተያዘ፣ እንዲሁ ተፈጥሮአዊ ሰው የሆነ፣ ያላመነ ያልተጠመቀ…….. እጅግ ብዙ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን አስተምራ አምና የመረቀቻቸው፣ ክህነት ድቁናና ቅስና የሰጠቻቸው፣ በጸጋ እግዚአብሔር ሰባኪ ሆነው የተለዩ ስብከቶቻቸውን የአውደ ምህረት ብቻ አድርገው ሊያዘጋጁ አይገባም፡፡ በለቅሶ ቤት፣ ሰርግ ቤት፣ ምዕመናን ቤት/ቤተሰባዊ ጉባኤ/፣ እንደ ፊሊጶስ /በሰረገላ /መጓጓዣ ውስጥ፣ ሴተኛ አዳሪዎች በሚሰበሰቡባቸው ቤቶቻቸው፣ ሰራተኞች ስራ ፍለጋ በጠዋት በሚኮለኮሉባቸው አደባባዮች፡፡ ሊስትሮ እያስጠረጉ ለሊስትሮዎች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ ለገበሬው በእርሻ ስፍራው በጽዋ ማህበራት፣ በሆስፒታል ይህን በመሰለ ቦታ የመዳን ወንጌል እንዲሰሙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጌታ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር እንደዚህ ነው የሰበከው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሐይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህን ኢየሱስን ተመልከቱ ብሎናል፡፡ዕብ 3፤1 በዚህ መንገድ ካልሰራን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤተክርስቲያን እንደ አውሮፓውያን አብያተክርስቲያናት የአረጋውያን ብቻ መሰብሰቢያ ልትሆን ትችላለች፡፡ መሪዎቿና ልጆቻቸው በቋንቋ እና በመረዳት/understanding/ የማይግባቡ በመካከላቸው ያለው ድልድይ የሰፋ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህን ተልዕኮ እየተቆጣጠረች ልትመራ ይገባታል፡፡ በዚህ መንገድ የስህተት ትምህርታቸውን በማስተማር ከመንጋው ለይተው ሜዳ የሚጥሉ ሰነፎች በዓለም በብዛት አሉና፡፡ በውጭ ያሉትን ካስተማሩ በኋላ ወደ በረቱ ማስገባት ግዴታ ነው፡፡ ሰብዓ ሰገልን የመራው ኮከብ ቤተልሔም አድርሷቸው እንደተሰወረ አገልግሎታችን በጎቹን አምጥቶ ለሞተላቸው ጌታ በቤቱ ማስረከብ አለበት፡፡ማቴ 2፤9 ምክንያቱም ጸጋው የሚገኝባቸው ሚስጢራት ማለትም ጥምቀት ቅዱስ ቁርባን ተክሊል ወ.ዘ.ተ በውጭ የማይፈጸሙ ናቸውና፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከውጭ የሚገቡት ውስጥ ከሚጠብቋቸው ምዕመናን ጋር መንፈሳዊ ህብረት መፍጠር አለባቸውና ነው፡፡ህብረቱ እስከ ጽዮን ተራራ እስከ ሰማይ የሚደርስ ነው፡፡ ይቆየን፡፡ዕብ 12፤22 ጌታ ሆይ ጉልበታችንን አበርታ እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት