Thursday, July 11, 2013

በዋሻው ውስጥ አገኘሁት




     ንጉስ ሳኦል ሊነግስ የተቀባውን ትንሹን ዳዊትን ያሳድድ ጀመረ፡፡ የልቡ አቅም የሚበልጠውን ሰው ሊታገሰው አልቻለም፡፡ ቀን ለአንዱ መንገስን ሲሰጥ ደግሞም ሊቀማ ይችላል፡፡ በተሰጠን በተሾምንበት ጸጋ ፣እድሜ ፣ገንዘብ፣  ከሰራንበት በኃላ እኛን የሚተኩ ሌሎች ይነሳሉ፡፡ እኛም ስፍራ ትተን ወደ መሰብሰቢያችን እንከማቻለን፡፡ ባለቀኖቹ በተራቸው ጊዜ የተሰጣቸውን አገልግሎት ከክብሩ ጋ  ይካፈላሉ፡፡ከአንዱ ከእግዚአብሔር ውጭ ዘላለማዊ ንጉስ የለም፡፡ ግን መተካቱን የማያመን ራሱን በራሱ ዘላለም ውስጥ ያስቀመጠ ሰው በእርሱ ፈንታ የሚተካውን ያሳድዳል፡፡ በቀለኛ ቀናተኛ ሆኖ ይቆማል፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ነገረ ገቢ ይሆናል፡፡በሃይማኖት ስም በሃሰት የሚከሱና የሚከሰሱ አገልጋዮች የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ ትናንት የነበሩ አገልጋዮች ዛሬ የመጡትን ደስ ብሏቸው ቢቀበሏቸው፣ በእኛ ዘመን ሁሉ ቀረ ዛሬማ…… በማለት አዲስ ገቢዎችን ባይንቋቸው እግዚአብሔር ሁሉን በጊዜ የሚሰራ አሳዳሪ መሆኑን ተረድተዋል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚያገለግሉ ይባላሉ፡፡ በቤተክርስቲያን አስተዳደር በሰበካ ወይ በቦርድ ሰው በራሱ ዘመን ብቻ ነው የሚሾመው ፡፡ሌላው ሲመጣ ዓለም አለፈ ነገር ተበላሸ ብሎ ካሰበ ራሱን አምላኪ ሆኗል፡፡ በገንዘባቸው አገልጋዮችን የሚያገለግሉ ሰዎችም ሌሎች ሲመጡ የቅናት ወይን እያሰከራቸው በተሾሙበት ገንዘብ ሊገዙ እንጂ ሊወዱ እንደሚገባቸው የሚረሱ እነሱ ያልተቆጣጠሩት ካህን ወይ ሰባኪ ህግ አልባ እንደሆነ አድርገው ማሰብ ይጀምሩና አሳዳጅ ለመሆን ማንም አይመልሳቸውም፡፡
     ሳኦል ዳዊት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋ እንደሆነ እና ባለድል እንደሆነ ተመለከተ፡፡ የሃገሩ ሴቶች አይናቸው በዳዊት ላይ አረፈ፡፡ ለህጻኑ ንጉስ መዝሙር ተደረሰ እልፍ ገዳይ ተባለለት ሳኦል እንዳይከፋው ሺህ ገዳይ ተባለ፡፡ ልዩነቱን እዩ!  እልፍ አስር ሺ ሲሆን ከሳኦል አስር እጥፍ አስበልጠውታል፡፡ በዚህ መዝሙር ሳኦል ተበሳጨ፡፡ ህጻኑን ንጉስ በያለበት ማሳደድ ጀመረ፡፡ ሊገድለውም በብርቱ ይፈልግ እና ይሰራ ጀመረ፡፡ ቀን የተካውን ሰው ቀን ባሳረፈው ሰው ፊት አብዝቶ ማመስገን ለሁለቱም ጉዳት ምክንያት ይሆናል፡፡ ተመስጋኙ ጠላት ያፈራበታል  ያልተመሰገነው ሰው ለከባድ ቅናት ይጋለጣል፡፡ ለዚህ ነው ውዳሴ ከንቱን መሸሽ የሚገባው ፡፡
     አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤- ሳኦል ዳዊትን ለመግደል በየተራራው እና ፍርኩታው ሊፈልገው ወጥቶ ወገቡን ሊፈትሽ ወደ ዓይን ጋዲ ዋሻ ገባ፡፡ በዚህ ጊዜ በዋሻው ማንም ይኖራል ብሎ ስላላሰበ በነጻነት ራሱን ሳይጠብቅ ወታደሮቹም ሳይከተሉት ተዘልሎ ተቀምጦ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊው ዳዊት ዋሻው ውስጥ ነበር፡፡ ሳኦልም ጉዳዩን ጨርሶ ሊወጣ ሲል፡ ዳዊት ዛሬ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ነበረ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም ብዬ ተውኩህ ብሎ ጮኧ፡፡ ሳኦልም እጅግ አምርሮ በራሱ አለቀሰ አንተ ጻድቅ ነህ እኔ ግን አመጸኛ ነኘ አለ፡፡1ኛ ሳሙ 24
   እኔም ጌታዬን በዋሻዬ ውስጥ አግኝቼዋለሁ! ሁል ጊዜ በክፉ ስራዬ አሳድደዋለሁ፡፡ እርሱ ወዳጄ ነው ቀብቶኛልና እግዚአብሔር የቀባውን እገድል ዘንድ እጄን አላነሳም ይለኛል፡፡ በእኔ ላይ ያለው የልጅነቴ ቅባቱ እንዳይጨክን ያደርገዋል፡፡  የሚያገኘኝ ወገቤን ፈትቼ ትጥቄን አውልቄ ፍርድና ሞት ይገባዋል በምባልበት የስንፍናዬ ሰዓት ነው፡፡ ራሴን ከጥፋት ማዳን በማልችልበት ጊዜ ነው፡፡ የምመካበት ሁሉ ሊረዳኝ የህሊናየን ባዶነት ሊሞላ በማይልችልበት ጊዜ ነው፡፡ ራቁቴን ለመሸፈን የራሴን ደርቆ የሚረግፍ ቅጠል ሰፍቼ ተሸሽጌ ሳለ ነው፡፡ በዋሻዬ የማገኘው ንጉስ ግን ሰይፍና ሃይል በእጁ የያዘ ቢሆንም ሊገድለኝ አይወድም፡፡ በሥራዬ ጠላቱ የሆንኩለት አርሱ እጅግ መልካም ነው! ምሮ ሲተወኝ አብዝቼ ከማልቀስ ሌላ አቅም አይኖረኝም፡፡ ለራሴ በሥራዬ የእግዚአብሔርን ልጅ መልሼ የሰቀልኩት በመሆኔ ከልቤ እነካለሁ፡፡ በመሸሸጊያዬ ውስጥ የእኔ ስንፍና እና የርሱ ምህረት ፊት ለፊት ሲተያዩ እመለከታለሁ፡፡  
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

No comments:

Post a Comment