Monday, August 5, 2013

ቅዳሴና ሥነ ስርዓቱ/ክፍል ሁለት/




    ባለፈው እንዳልነው ቅዳሴ ከጌታችን ጋር የምንገናኝበት ልዩ አገልግሎት እንደመሆኑ ሁሉም ሰው በፍርሃት እንዲቆም ይታዘዛል፡፡ በጸሎቱም መጀመሪያ ካህኑ ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት ይህች ሰዓት ምን ያህል የምታስጨንቅ ናት መንፈስ ቅዱስ ከሰማያት የሚወርድባት መስዋዕቱን የሚያከብርባት በፍርሃትና በጽሞና ቁሙ የእግዚአብሔር ሰላም ከእኔና ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ ጸልዩ ይላል፡፡
    ጸሎቱ በአምስት ልዑካን የሚመራ ቢሆንም በአንዳንድ የውጭ ሃገራት በሁለት በሶስት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ካህን ቅዳሴውን ይመራና ሥጋውን የመፈተት ሥራ ያከናውናል፡፡ ሁለተኛው /ንፍቁ ካህን/ ዋናውን ካህን ይራዳል ነገር ግን እርሱም ለራሱ ተመደበውን ጸሎት ይመራል፡፡ዲያቆናቱ እንዲሁ አንደኛው የሚጸልየው ጸሎት ያለው ሲሆን በአብዛኛው ምዕመናን በቅዳሴው ተካፋይ እዲሆኑ ተንስኡ ለጸሎት እያለ ለጸሎት ያነቃቃል፡፡ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን ሰላም ስለህዝብ ሁሉ የሚጸለየውን ጸሎት ይመራል፡፡ ሁለተኛው /ንፍቁ/ ዲያቆን የቀረውን ለእርሱ ተመደበለትን ጸሎት ይጸልያል፡፡ ሦስተኛው ዲያቆን ድምጽ ማጉያ ይይዛል፣ እጣን ያስባርካል በወንጌል ሰዓት ዣንጥላ ይዘረጋል፣ እጅ ያናፃል/ያስታጥባል/፡፡
     ዲያቆናቱ በእጃቸው መብራት ይይዛሉ፡፡ ይህም በመገናኛው ድንኳን ሳይጠፋ ሁልጊዜ ይበራ እንደነበረው መብራት አይነት ነው፡፡ አገልግሎቱም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሲሆን በገጠር ደግሞ መብራትም ሆኖ መቅደሱን ያደምቃል፡፡
     ካህናቱ ጽና ይዘው እጣን ያጥናሉ፡፡ ይህ ቀጥታ ከሰማዩ ስርዓት የተወሰደ ነው፡፡ ዮሐንስ በራዕይ መላዕክቱ የቅዱሳንን ጸሎት ለማሳረግ እጣን እንደያዙ አይቷል፡፡ራዕ8:4 በእርግጥ እግዚአብሔር ሁሉን በያሉበት ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን አምልኮ ለክብሩ ስለሆነ ጌትነቱን ለማሳየት ይሄ ስርዓት ተዘጋጅቷል፡፡ በመንበሩ ዙሪያ ለመሪዎች ለቤተክርስቲያን ለሙታን ጸሎት ሲደርስ፣ ካህኑ ንስግድ ብሎ ሲያዜም ስግደቱን ለማሳረግ፣ ወንጌል ሲነበብ፣ ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግስትከ ብለን ስንጸልይ፣ እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ ብለን ስንማልድ እጣኑ ወደ ላይ ያርጋል፡፡በዚህም የህዝቡ ጸሎት ያርጋል፡፡ራዕ 8 2-4
    ቅዳሴው ጥንታዊ በመሆኑ በግዕዝ ቋንቋ የተደረሰ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግዕዝ በዛ ዘመን የመግባቢያ ቋንቋ ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ግን በከፊል ወደ አማርኛ ወደ እንግሊዝኛ እንዲሁም ወደ ኦሮምኛ እየተተረጎመ ነው፡፡የሚፈጀውም ሰዓት እንደ ድርሰቱ ቢለያይም ከአንድ ሰኣት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሳያዜሙ በንባብ ያሉት እንደሆነ አንድ ሰዓትም ሊበቃው ይችላል፡፡ ቤተ መቅደስ በሰዓት ተከራይተው የሚገለገሉ ምእመናን ባሉበት በውጭ ሃገር እንደ ሃገር ቤቱ በዜማ ላይቆይ ይችላል፡፡ ጊዜ ኖሮ በሙሉ ዜማው ቢጸለይ ግን ከእግዚአብሄር ጋር የምንቆይበት ሰዓት አጭር አይሆንብንም፡፡
    ክርስቲያኖች የራሳቸውን ድርሻ በቃላቸው አጥንተው ወደ ቤተመቅደስ ገብተው ከካህናቱ ጋር ቅዱስ ብለው እንዲያስቀድሱ ብዙ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ይህ ለማድረግ ትናንሽ የተስጥኦ መቀበያ መጽሐፍትን መግዛት ይጠበቀባቸዋል፡፡ በውጭ  ሃገራት ባሉ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት  በፕሮጀክተር እና በስክሪን ቅዳሴን ከነተሰጥኦው ፊት ለፊት ማየት ስለሚቻል ህዝቡ የራሱን ድርሻ በቀላሉ መማር አይቸገርም፡:
    በቅዳሴ ሰዓት የበረታ ቆሞ የደከመ ተቀምጦ ያስቀድሳል፡፡የራስ ጨዋታ የስልክ ድምጽ በጋራ ጸሎት ጊዜ መጠቀም በጥብቅ ተከለከለ ነው፡፡ ጌታችን ሁለት ሦስት ሆናችሁ በስሜ ብትሰበሰቡ እኔ በመሀላችሁ እገኛለሁ ያለውን የታመነ ኪዳን ሊፈጽም አብሮን የሚሆንበት ሰዓት ነውና ፍርሃትና አክብሮት ሊኖረን ይገባል፡፡ 
    አንዳንድ አማኞች በስራ ሲደክሙ አምሽተው በሚገባ ሳያርፉ ሌሊት ወደ ቅዳሴ ይመጣሉ፡፡ መጥተውም አሃዱ አብ ተብሎ እትው በሰላም እስኪባል ያንቀላፋሉ፡፡ እንደዚህ መሆን ግን የለበትም፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የምንቆምበት ሰዓት ውድ ነውና በቂ እረፍት ወስደን ተዘጋጅተን መምጣት ይገባል፡፡ሌላው መታወቅ ያለበት አቢይ ቁም ነገር የምናስቀድሰው ቅዳሴ ጠበል ጠጥቶ አሜን ብሎ ለመመለስ ብቻ አይደለም ሥጋውን ለመብላት ደሙን ለመጠጣት ነው እንጂ፡፡  ሁሌ አስቀዳሽ ግን ቁርባን የማንፈራ እንዳንሆን ስለቁርባን በቂ ትምህርትና ግንዛቤ ለማግኘት መጣር አለብን፡፡
    አዲሱ ትውልድ በወንጌል መርሃ ግብር ላይ ነቅሎ መውጣት ነገር ግን በጋራ ጸሎት ላይ በተለይ በቅዳሴ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ሲያቅተው ይታያል፡፡ በእርግጥ ወንጌል መስማት መዝሙር መዘመር በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ተግባራዊ አምልኮ ግን ያስፈልጋል፡፡ ተግባራዊ አምልኮ  ሥጋን  የሚያደክም ቢሆን እንኳ ስደክም ያን ጊዜ ሃይለኛ እሆናለሁ እንደተባለ ጸጋው ብርቱ ያደርጋል፡፡2ኛ ቆሮ 12፡9
  ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ማለትም ከቅዱስ ቁርባን ከጋራ ጸሎት መካፈል ደግሞ በፍቅር የሆነ አምልኮ ሰለሆነ ከዝለት ይጠብቃል፡፡ በእጃችን የምንይዘው ስልክ ቻርጅ ካላደረግነው እንደማይሰራ ሁሉ በጸሎት ያልሞቀ በቅዱሳት ሚስጥራት ያልተቀደሰ ሰውነት በቀላሉ ተሸናፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሌሎች ሼር አድርጉት 



No comments:

Post a Comment