Thursday, July 11, 2013

ቅዳሴ ምንድን ነው?




ቤተክርስቲያናችን ወደ አምላኳ ከምታቀርባቸው ጸሎቶች አንዱና ዋናው ጸሎተ ቁርባን ወይም ቅዳሴ ነው፡፡ ይህ ጸሎት ጌታ በጸሎተ ሐሙስ ከሀዋርያቱ ጋር ያደረገውን የቁርባን ጸሎት የመሰለ ነው፡፡ በተለምዶ ቅዳሴ ይባላል ስሙ የሚቀደስበት፣ ብዙ ምስጋና የሚቀርብበት የአምልኮ ጸሎት በመሆኑ እንዲህ ተብሏል፡፡ ጸሎቱ አንክሮ /ስለ አምላክ አድናቆት/ ምስጋና፣ ምልጃ፣ትምህርት በአንድ ላይ የተቀናበሩበት ነው፡፡ ቅዳሴው በተለያዩ ደራስያን የተደረሰ ሲሆን በጣም መንፈሳዊ ነው፡፡ ጸሎቱ ሁሉ በአንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በርሱ ያለ ክብር እና ጽን/ብርታት/ ላንተና ለመንፈስ ቅዱስ ይገባል እስከ ዘላለም በማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የታሰረ ነው፡፡ ጌታ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ ይሰጣችኃል ያለውን የተስፋ ቃል ማዕከል አድርጓል፡፡ዮሐ 16፡24
      ቅዳሴ አማኞችን ከእግዚአብሔር ጋር ሊያገናኝ የሚችል ብርቱ ጸሎት ነው፡፡ ጸሎቱ የሚጀምረው መስዋዕቱን ካህናት እና ዲያቆናት ከቤተልሄም አክብረው ሲገቡ ነው፡፡ ማርያም ድንግል እና ቅዱስ ዮሴፍ ሊቆጠሩ ወደ ቤተልሔም ወርደው  በዛም አዳኙ ተወለደ፡፡ የሰው የመዳን ጉዞ ከዛ ተጀምሯል፡፡ በጉ በበጎች በረት ተወልዷል፡፡ ስለዚህ ቅዳሴው ከቤተልሔም ተጀምሮ ወደ መቅደስ በቃጭል ድምጽ ታጅቦ ይገባል፡፡ የተወለደው ህጻን በመላዕክት መዝሙር በዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነት ታጅቦ ወደ አለም እንደገባ ያሳያል፡፡ ቤተመቅደስ ከገባ በኃላ መንበሩን እየዞረ ወደ መሰዊያው/ታቦቱ/ ላይ ያርፋል፡፡ ጌታም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ እየዞረ የመንግስትን ወንጌል አስተምሮ ወደ መሰዊያው ወደ መስቀል መጓዙን የሚያሳይ ዑደት ነው፡፡ ታቦት እና ጽላት በሃዲስ ኪዳን ትርጉሙ አንድ ነው አገልግሎቱም ስጋውና ደሙ የሚሰዋበት የሚያርፍበት መሆኑ ነው፡፡በዚህ ሰዓት ከምስጋና ከአምልኮ ጸሎት በተጨማሪ ስለብዙዎች ጸሎት ይቀርባል፡፡ በቅዳሴ ላይ ስማቸው የማይነሳ የማይጸለይላቸው ሰዎች በምድር ላይ የሉም፡፡ ላላመኑ ሰዎች እንኳ ትንሳኤ ልቦና እንዲያገኙ ይለመንላቸዋል፡፡
    ስለመሲሁ መምጣት የተገሩ የዳዊትን መዝሙራት በመሃል ቅዳሴው ላይ ዲያቆኑ በዜማ ይሰብካል፡፡ ተስፋ የተነገረለት አዳኝ በሥጋ መገለጡንና የምሥራቹን መስበኩን ለማሳየት ከወንጌል እለቱን የተመለከተ ምንባብ ይነበባል፡፡ ከዚህ በኃላ ወደ ፍሬ ቅዳሴ ወደ  ቁርባኑን   ጸሎት ይገባል፡፡
      ሃበነ ንኅበር በሚለው ጸሎት ህብስቱ ወደ ሥጋ አምላክ ወይኑ ወደ ደመ መለኮት ይቀየራል በእምነት፡፡ ጌታ ህብስቱን አንስቶ ባረከ እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው ብሉ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ  ስለብዙዎች ኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ ደሜ ነው ማቴ 26፡26 ያለውን ቃል መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ጌታ አመስግኖ በሰጣቸው ጊዜ ህብስቱ ሥጋ ወይኑ ደመ ኢየሱስ ወደ መሆን ተቀይሯል አማኞች ሞቱን መነሳቱን እያሰቡና እየመሰከሩ ይበሉታል ይጠጡታል፡፡ ከተለወጠ በኃላ ካኅኑ ለእርሱና ለህዝቡ ኃጢአት በመሰዊያው ፊት ሥጋውን በእጁ ይዞ የምልጃ ጸሎት /እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ/ ብሎ ኃጢአትን ይቅር ወደ ሚል ወደ ዳዊት ልጅ ወደ ኢየሱስ ክረስቶስ ይለምናል፡፡ አማኞች ከተጠመቁ በኃላ ለነፍሳቸው ምህረትን በመስቀሉ ቢያገኙም በሥጋ ወራት በሚሰሯቸው ሃጢአቶች እስከሞት ድረስ ሊያደርስ የሚችል ቅጣት ሊያመጣ የሚችል በደል ሊሰሩ ይችላሉ /ሐናንያና ሰጲራን ይመልከቱ የሐዋ ሥ.5፡1-6 /ስለዚህም ንስሃ እና በቁርባን ስርየት ያስፈልጋቸዋል …..እላችኃለሁ ንስሃ ባትገቡ ሁላችሁ ትጠፋላችሁ 13፡ 3 እንዲሁ የእግዚአብሔር መንግስት ልብሳቸውን በበጉ ደም ያጠቡ ብቻ ይገቡባታል፡፡ አምስቱ ውሾች የተባሉ በኢየሱስ ያመኑ ቢሆኑ እንኳ ወደ ደጆቿ እንዳይገቡ የተከለከሉ አሉ፡፡ እነዚህም አስማተኞች፣ ዘማውያን፣ነፍሰ ገዳዮች፣ጣዖት አምላኪዎች የሐሰትን ስራ የሚወዱ ሁሉ ናቸው ራዕ 22፡15
     ስለዚህ ደሙ እነዚህን በእግዚአብሔር ፊት እንዲያቆማቸው እና እንዲቀድሳቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ሰው በፍላጎቱ ጎትቶ የሚመጣው እድፉ በደሙ ይታጠባል፡፡ ቁርባኑ አማኞችን ከመቅሰፍት የሚጠብቅ እንደሆነ ሁሉ አዲስ ተጠማቂዎችን ወደ ክርስቶስ አካልነት ያመጣቸዋል፡፡ በሥጋው በኩል ሁሉም አንድ አካል በመሆን ራስ ወደ ሚሆነው ይጋጠማሉ፡፡ በነፍሳቸው የዳኑ ስለመሆናቸው ይመሰክርላቸዋል፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው ተብሎ ተጽፏል፡፡ 1ኛ ዮሐ5፤10 አንዳንድ ሰዎች ተሰቀለ ሞተልኝ ብዬ ካመንኩ መቁረብ አለመቁረብ ጥቅሙ ምንድነው ብለው ኢየሱስ ያስቀመጠውን እውነት በራሳቸው አመለካከት ማስተካከል ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሥጋ አሰራር የማይመቹ መንፈሳዊ ስርዓቶችን አብዝተው ይቃወማሉ በአምኛለሁ ስም ከለመዱት የኃጢአት ልምምድ ጋር መቆየት እና በኢየሱስ ከዳንኩ ምን ቸገረኝ አይነት አስተሳሰብ ያጠመዳቸው ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ካስተማረው ወንጌል ይልቅ ለአህዛብ ማቅረቢያ የተጻፉትን የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክታት ብቻ በራሳቸው ፍላጎት አጣመው መጥቀስ ይወዳሉ፡፡ ካህን አያስፈልግም ቁርባን መታሰቢያ ብቻ ነው በማለት ተግባራዊውን እውነት ይቃወማሉ፡፡እምነት ተግባራዊ ነው ከከንፈር ያለፈ ከልብ የፈሰሰ ተግባር የሌለው ከሆነ በራሱ የሞተ ነው ይላል ያዕቆብ፡፡መቁረብም ንስሃ መግባትም መጠመቅም ማልቀስም ለሰው በፍቅር የሆነ ሥራም በአፍ ሳይሆን በተግባር የሚሰራ ነው፡፡ እምነት ከልብ ነው ለእምነት መታዘዙም በተግባር ነው ፡፡ያዕ 2፡14 እንዲያ ካልሆነ አጋንንታዊ እምነት ይሆናል፡፡
     ቅዳሴው የሚገባደደው እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ በሚለው የምልጃ ጸሎት ነው፡፡ ሰውና እግዚአብሔር በደሙ ከተያዩ በኃላ ዲያቆኑ ነአኩቶ በሚለው የምስጋና መዝሙር እግዚአብሔርን ያከብራል፡፡ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ከሰጠ በኃላ አብረው ዘምረው ወደ ደብረዘይት እንደወጡ/ማቴ 26፤28/ ሁሉ ዲያቆኑ ነአኩቶ ለእግዚአብሔር ቅድሳቶ ነሢአነ ከመ ለሕይወተ ነፍሰ ይኩነነ ፈውሰ….. ሥጋውና ደሙን ተቀብለን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን ለነፍሳችን አኗኗር መድሃኒት ይሆን ዘንድ የተቀበለን እኛ አምላካችንን እያመሰገንን እንለምናለን አደራም እንላለን ይላል፡፡ ካህኑም ስብሐተ እግዚአብሔር ይነግር አፉየ ….አንደበቴ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል የሥጋ ሁሉ ፍጥረት ቅዱስ ስሙን ይባርክ ይላል፡፡ ህዝቡም በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ወደ ፈተና አታግባን ብሎ በደሙ መቀደሱን እንዲጠብቅ እንዲረዳው ይለምናል፡፡  ቅዳሴው በቡራኬ ይጠቃለላል፡፡ ይቀጥላል
ለሌሎች ሼር አድርጉት

1 comment:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ! ግን ባክግራውንዱ ጥቊር ባይሆን ነው የሚሻለው

    ReplyDelete