Thursday, July 11, 2013

ፍቅር



        
    ፍቅር - ፍቅር የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መቀራረቢያ ሃይል ነው፡፡ይህም ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ ስሜታዊና መንፈሳዊ፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ እብድ ሲሆን ሁለተኛው ሰከን ያለው ነው
 እብድ ፍቅር - የአፍቃሪውን ስሜት ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠራል፡፡የዳዊት ልጅ አምኖን የተያዘው በዚህ አይነት ፍቅር ነበር፡፡ አምኖን ወዳጁ ኢዮናዳብ ከፊቱ የደረሰበትን ጉዳት መለየት እስኪችል ድረስ ስር በሌለው ፍቅር ተጎድቶ ነበር፡፡2 ሳሙ 13 እንዲሁ በዚህ ፍቅር የወደቀ ሰው ምግብ አይበላም መተኛት ይሳነዋል፡፡ካፈቀረው ሰው በስተቀር ለማንም ግድ የለውም፡፡ ወንድ ከሆነ የወደዳት ልጅ ለእርሱ ሙሉ ዓላማው ነች ስለዚህ ከማንም ጋር ስልክ እንድታወራ ወደ ቤተሰቦቿ እንድትሄድ ጓደኞቿን እንድታገኝ አይፈልግም፡፡ ሙሉ ቀን እርሱን ብቻ እንድታሰብ ይፈልጋል፡፡ ሴቷም እንዲሁ፡፡ሲገናኙም አንዳቸው የአንዳቸውን አይን እያዩ ያወራሉ፡፡በአካባቢያቸው እሳት አደጋ እንኳ ቢፈጠር ከሌላ ሰው ዘግይተው ነው የሚነቁት፡፡ስቃይ የተሞላ ደስታ ይደሰታሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወቀሳ ያበዛሉ፡፡ ረስተሸኛል ትተሸኛል ጠልተሸኛል ይላል፡፡ እርሷም እንደሚወዳት ብታውቅም በጣም ከማፍቀሯ የተነሳ ለኔ ግድ የለህም አትወደኝም ….ትናንት የደወለችው ማነች? /ምናልባት ዘመዱ ልትሆን ብትችልም/ የመሳሰለ ጥያቄ ታበዛለች፡፡ አብሯት እየሄደ እያለ ማንንም ቀና ብሎ እንዲያይ አትፈቅድም ሁሌ ጎንበስ ብሎ እንዲራመድ ትፈልጋለች፡፡ ሁለቱም በወቀሳ መፈቀራቸውን እርግጠኛ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ይሄ ፍቅር ስግብግብ ነው ለእኔ ብቻ! ያሰኛል፡፡ እኔን ብቻ እግኚ፣እኔን ብቻ አስብ፣ለኔ ብቻ ደውይ፣ እኔን ብቻ ተመልከት እኔን ብቻ አውሪኝያበዛል፡፡ ለብዙ ወራት በጥንቃቄ በስሜታዊው ፍቅር የቆየ ሰው ያስለመደውን አንድ ቀን ቢያጎድል /ምናልባት ቀኑን ሙሉ ካልደወለ/ ተዓምር የተፈጠረ አድርጎ ያሳያል፡፡ ኩርፊያውና ጥሉ መብረጃ ያጣል፡፡ሌላ ሶስተኛ ሰው እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ልታስታርቋቸው ብትሞክሩ አይ ሞቼ እገኛለሁ ብለው ለገላጋይ ያስቸግራሉ፡፡ አንዳንዴ በተለይ ሴቶቹ ለጓደኞቻቸው አፍቃሪያቸውን ሙልጭ አድርገው ያማሉ ያሳማሉ፡፡ ክፉ ካናገሩ 15 ቀን በኃላ አብረው ታገኟችኃላችሁ፡፡ እንደውም ባለፈው እኮ የተጣላን ጊዜ ጓደኛየ ካንተ እንድለያይ መከረችኝ እኔ ግን በጭራሽ አልኩ ብላ ፍቅሯን ታደምቅበታለች፡፡በእውነት ይህ እብድ ፍቅር ነው፡፡ በብዛት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚከሰት ሲሆን ሰፊ ጊዜ ባላቸውና በሥራ ባልተጠመዱ ሰዎች ቤት በብዛት ይገኛል፡፡ ስሜታዊው  ፍቅር እንደ እሳት የሚቀጣጠለው በልብ ወለድ መጽሐፍትና በሙዚቃ ነው፡፡ የትኛውም ዘፈን ላፈቀረው ሰው ትርጉም እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡ስለዚህ ቀኑን ሙሉ ዘፈን ጆሮው ላይ አድርጎ ይውላል፡፡
   ይህ ፍቅር ስሜት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ስሜትን ሰድሮ ይይዛል፡፡ ጣፋጭ ወይን ሲጠጡት የሚያሰክር አይመስልም ነገር ግን ከመቀመጫ ሲነሱ እግርን ያብረከርካል፡፡ ይሄ ፍቅር እንደዚህ ነው፡፡ ልብ የሚደነግጥለትን ሰው አትኩሮ በመከታተልና አብዝቶ በማሰብ ፍቅሩ ሊቀጣጠል ይጀምራል፡፡ ይሄ ፍቅር እውር ነው፡፡ በዚህ ፍቅር የተያዘ ሰው በልጅነታችን ዓይናችንን አስረን የምንጫወተውን ያዕቆብ የተባለ ጨዋታ የሚጫወትን ሰው ይመስላል፡፡ አምኖን የአባቱን ልጅ ትዕማርን ያፈቀረው አይኑ ተከፍቶ ይመስላችኃል?  1ኛሳሙ13;2  እብዱ ፍቅር ማየት አይችልም፡፡ ሚስት በቤቱ እያለችው ከስራ ባልደረባው ጋር ቅልጥ ያለ ፍቅር ይይዘዋል፣ ከማያም ሰዎች ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ረስታ በእምነት ከማይመስላት ጋር ልሙትልህ-ፍቅር ይይዛታል፡፡ ትንሹ ልጅ እናቱ ከምትሆን ትምህርት ቤት አስተማሪው ወይም  ከቅርብ ዘመዱ ጋር በአይን ፍቅር ይወድቃል፡፡ ይሄ ፍቅር አይን አለውን? በፍጹም!
     ይሄ ፍቅር በደንብ ካልያዙት ጨካኝ ነው፡፡ የሚፈልጋትን ልጅ ያጣ እንደሆነ በራሱ ላይ ጨካኝ ርምጃ ይወስዳል ወይም ልጅቷን ይጎዳል፡፡በስሜታዊ ፍቅር ተይዘው በራሳቸው ዓለም ተጋብተው ልጅ ከመጣ በኃላ አላውቅሽም ብሎ የሚክደው ጨካኝ ስለሆነ ነው፡፡ ራስ ወዳድም ነው እንደ አምኖን የወደዳትን አታሎ ያጠቃል፡፡1 ሳሙ13;14 በሴት ጓደኞቻቸው ላይ አሲድ የሚደፉ ወጣቶች፣  የሚፈልጉትን አድርገው የሰውን ህይወት ከጎዱ በኃላ ፊታቸውን የሚያዞሩ የእብዱ ፍቅር ውጤቶች ናቸው፡፡የዚህ ፍቅር እድሜ የስርቆሽ ካልሆነ ቢበዛ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ምናልባት የስርቆሽ ከሆን ትንሽ ዘመኑ ሊገፋ ይችላል፡፡በዚህ ፍቅር ውስጥ ማስተዋል የሚባለው የመንፈስ ፍሬ አይገኝም፡፡ስለወደዳት ልጅ ክፉ ጎን ለማየት ይቸገራል፡፡ ዋናው ፍቅሩ ነው የሚል ፍልስፍና ይከተላል፡፡የወደድኳት ልጅ ነገ ለህይወቴ አጋር መሆን ትችል ይሆን የሚል ሚዛናዊ እይታ ይጎድለዋል፡፡ ዛሬ ወዷታልና የዘላለም ገነቱ ትመስለዋለች፡፡ ለጸሎት ሲቆም እንኳ ጌታ ሆይ ይህችን ልጅ ፍቃድህ ከሆነ የኔ አድርጋት ፍቃድህ ካልሆነም የኔ አድርጋት ብሎ የጌታን ፍቃድ ሳይሆን የራሱን ፍቃድ ይለምናል፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቃድ ባለማስተዋሉ ሞኝ ሆኗል፡፡ኤፌ517

No comments:

Post a Comment