Friday, March 28, 2014

battery low- ሃይል አለቀ የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡

battery low- ሃይል አለቀ የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡ ትደክማለች፡፡ ከሃይሏ ከተለያየች battery low ትላለች፡፡በጋለ ፍላጎት እናመልክ ከነበረ መንፈሳችን ሙትት ይልብናል፡፡ መጸለይ አሰልቺ ሥራ ይሆንብናል፡፡ ቃል ወደምንሰማበት ጉባኤ ለመሄድ ፍላጎት ስለምናጣ አገልግሎቱን እንተቻለን፡፡ ምን እነሱ ሰዓት አያሳጥሩ! የሚሰብኩት በግዕዝ ነው አይገባ! ወ.ዘ.ተ. ቅያሜ ለበስ ንግግሮች እናበዛለን፡፡ ይሄኔ ነፍሳችን battery low እያለችን ነው፡፡ ጓደኞቻችን ስለፓለቲካ፣ ስለኳስ ፣ ስለጌጣጌጥ የሚያወሩ ብቻ ቢሆን ደስ ካለን፣ መንፈሳዊ ሃሳብ ካላቸው ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ ከወደድን ሃይላችን እያለቀ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ያነበብናቸው መጽሐፍት ፍልስፍናና ልብወለድ ብቻ ከሆነ ብዙ ጊዜያችንን ሙዚቃ በማዳመጥ ካሳለፍን ድሮ የነበረን የሞቀ ልባችን ከቀዘቀዘ battery low እያለን ነው፡፡ ወንጌልን በመረዳት ስም ከተግባራዊ አምልኮ ማለትም ለብርቱ ጾም፣ ከጸሎት፣ ድሆችን ከመጎብኘት፣የተቀቡትን ከማክበር ፣ ንስሃ ገብቶ በራስ ስንፍና ከመጸጸት ይልቅ በቃል መደባደብን ከመረጥን ቀይ መብራት እያበራን ነው፡፡ ሌሊት ተነስቶ ማስቀደስን ከተውን፣ ለራሳችን ልዩ ጊዜ ካጣን፣ ከንስሃ አባቶቻችን ጋር የመገናኘት ፍላጎታችን ከሞተብን ነፍሳችን ባትሪ እየጨረሰች እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ወርቃማ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ህይወት ትኩር ብሎ መመልከት ካቃተን፣ ስዕሉ ከህሊናችን ከጠፋ ይህ በመሆኑም ምንም ካልመሰለን ወደ ራሳችን ማየት እንዳለብን ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ሁሌ ትችትና ንቀት የተሞላ ሃሳብ ከልባችን ከወጣ ልባችን ታውቃለህ፣ ትበልጣለህ፣ ሌሎች ግን አይረቡም፣ አያውቁም፣ አልተረዱም ካለን battery low እያለን ነው፡፡የዓሳ አጥማጁን የጴጥሮስን የዋህ ልብ ጥለን የመጽሐፍት ሸምዳጁን የቀያፋን ልብ በውስጣችን ካገኘን አደጋ ላይ ነን፡፡ መቅረዙ የተወሰደበት መብራቱ የጠፋበት ሰው ሆኖ መኖር ምቾት ይሰጣል? በሞተ ህሊና በደነዘዘ ልብ መመላለስ ያስደስታል? የድንኳናችን/ሰውነታችን/ መብራት ጠፍቶ እስከመቼ ይኖራል? እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅክ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ስራህን አድርግ፡፡አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡ ራዕ 2፤5

No comments:

Post a Comment