ሰላም ለሁላችሁ፤- በእግዚአብሔር
ቅናት እቀናላችኋለሁ እንደንጽህት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፡፡ 1ኛ ቆሮ 11 ያመኑ ሁሉ
በመጨረሻው ሰርግ ወደ መንግስቱ ተሞሽረው እንዲገቡ በደም ቀለበት ታጭተዋል፡፡እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ ያለው ዓላማ ሁሉ ለክርስቶስ
እንዲሆኑ ነው፡፡ የሰውም መንፈሳዊ እድገት የሚሄደው ክርስቶስን ወደ መምሰል ነው፡፡ ማንም ራሱን መስሎ እና የራሱ ሆኖ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ ራሱን እንዲመስል የተፈቀደለት የመጀመሪያው ሰው አፈር
መስሎ ተበላሽቷልና፡፡እናንተ ወደ ማን እየተጓዛችሁ ነው? ምኞታችሁስ ማንን ለመምሰል ነው? የነፍሳችሁ ራስ/ባል/ ማነው? ሙሽርነታችሁስ
ለማን ነው? የምትኖሩት እና የምትሞቱት ለማን ነው? የመኖራችሁ ዓላማ ምንድነው? ክርስቶስ ኢየሱስ አይደለምን? እርሱን እንደ ባዕድ
እና ትርፍ መጠጊያ አድርጎ ማሰብ ከእናንተ ይራቅ! እርሱ ሁለተኛ ወይ ሦስተኛ ምርጫ የሆነላት ነፍስ ሚዛኗን ታስተካክል፡፡ ሁለትና
ሦስት ባል ያገባች ሚስት አንዱን ብቻ ታግባ! በሏን ለብ አድርጋ የምትወድ ሚስት ባሏን በደንብ መውደድ እንደሚገባት ሁሉ ለታጨንለት
ጌታ እውነተኛ ሙሽሮች ፍቅረኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
Tuesday, July 16, 2013
Thursday, July 11, 2013
አማርኛ መዝሙራት
መዝሙር አንድ መንፈሳዊ ሃሳብ በዜማ ተዋህዶ በጆሮአችን የምንሰማው
እግዚአብሄርን የምናመልክበት፣ስለጌታችን አዳኝነት፣ ስለቅዱሳን ፣ስለቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም ስለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትምህርት የምናገኝበት
የጸጋ ስጦታ ነው፡፡መዝሙር ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጀምሮ ጥቅም ይሰጥ ነበር፡፡ የያዕቆብ ልጆች የኤርትራን ባህር በተዓምራት እንደተሻገሩ
የሙሴ እህት ማርያም ከበሮ ይዛ ከህዝቡ ጋ ለእግዚአብሄር ዘምረዋል፡፡ዘጸ 15፤21 ዳዊትም ታዋቂ ዘማሪና በገና ደርዳሪ ነበር፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የሚገነዘበውንና በልቡ የሚሰማውን በመልክ አደራጅቶ ዘምሯል፡፡ማቴ 26… በሃዲስ ኪዳንም የሁላችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
እግር ባጠበበት ምሽት ከደቀመዛሙርቱ ጋር ከእራት በኃላ ዘምሯል፡፡ዮሐ… እነ ቅዱስ ጳውሎስም በእስር ቤት ዘምረዋል፡፡የሐዋ .ሥ
16
በኢትዮጵያም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ቅድመ ቅዱስ ያሬድ አምልኮተ
እግዚአብሄር ይፈጸም ስለነበር መዝሙር ይኖር እንደነበር ይገመታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በ6ኛው ክፍለ ዘመን ሲነሳ መልክ ያለው ዜማ ከድርሰቱ
ጋር ለቤተክርስቲያን አዘጋጅቷል፡፡ያም እስከ ዛሬ ድረስ ቤተክርስቲያን በየበዓላቱ ስብሐተ እግዚአብሄር የምታቀርብበት የቁርባን ጸሎት/ቅዳሴ/
የምትጸልይበት ድንቅ ዜማዋ ሆኗል፡፡
መዝሙር በዘመናችን
ዘመናዊው ዓለም ሁልጊዜ የራሱን ቋንቋ የሚናገር ነውና በዘመናዊው ዓለም
ባሉ አማኞች ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ የሚናገሩ ሌሎች ቤተእምነቶች በሚያዘጋጇቸው የተለያዩ መዝሙራት እየተሳቡ ከቤተክርስቲያን የሚሰደዱ
ሚሊየኖች እየበዙ ሲመጡ የቤተክርስቲያን ወጣቶች ያንን ሊተካ የሚችል በዜማ የተሰሩ መዝሙራትን በየሰንበት ትምህርት ቤቱና በካሴት
እያዘጋጁ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ እነመሪጌታ ጸሐይ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ወደ ሌላ ቤተ እምነት
መፍለሳቸውን መተው ጀመሩ፡፡
አልፎ አልፎ በካሴት የሚዘጋጁ መዝሙራትን በተመለከተ ሁለት አመለካከቶች
ይሰማሉ፡፡ቆየት ያለውን የቅዱስ ያሬድን ዜማ ያስረሳል የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ዜማው ሊረሳ የሚችለው የካሴት መዝሙራት ስለመጡ
ሳይሆን በዜማው ላይ የተሾሙ ሰዎች ምዕመናንን በሚመጥን ሁኔታ ዜማውን ማስተማር ባለመቻላቸው ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በቀላሉ
ትውልዱ እንዲማረው ማድረግ የሊቃውንት ሃላፊነት ነው፡፡ ያንን ሳያደርጉ ቸል ቢሉ የካሴት መዝሙራት ኖሩም አልኖሩም ዜማው እየተረሳ
መምጣቱ አይቀርም፡፡ከዚህ ሃሳብ በተቃራኒ የቆሙት ተከራካሪዎች ደግሞ የቤተክርስቲያን አገልግሎት በቅኔ ማኅሌትና በቤተ መቅደስ ብቻ
የሚገደብ አይደለም፡፡ በስብከተ ወንጌል አዳራሾች፣ በማህበራዊ ሕይወት/በሰርግ በኃዘንና በደስታ/ እንዲሁም በተለያዩ ሥፍራዎች የሚደረገው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሁሉ የቤተክርስቲያን አገልግሎት
ነው፡፡ ስለዚህም የአማርኛ መዝሙራት በአፍአ/በውጭ/ ያለውን አገልግሎት ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ሚና አለው ይላሉ፡፡/የአማርኛ
መዝሙራት- መምህር ሰሎሞን ዘማህበረ ቅዱሳን/
የካሴት መዝሙራት
በእርግጥም የካሴትና የሰንበት ትምህርት ቤት መዝሙራት በዚህ ዘመን
መኖራቸው እንደማዕበል ባጥለቀለቁን የሌሎች ቤተ እምነት መዝሙራት ተስበው የሚወጡ አማኞች በቤተክርስቲያን እንዲቆዩ ትልቅ አስተዋጽኦ
አድርጓል፡፡እንዲሁም አማኞች ስለእምነታቸው ግዛቤ እንዲያገኙ፣ በተመስጦ ንስሃ እንዲገቡ፣ ከአምላካቸው ጋር በህሊና እንዲገናኙ፣
ሃዘንን እንዲረሱ፣ መንፈሳቸው እንዲበረታ ትልቅ እገዛ አድርገዋል፡፡በተለይም በገጠሪቱ ሃገራችን ያሉ ምዕመናን ሰባኪ የማግኘት እድል
የላቸውምና ወጣቶቹ በየሰንበት ትምህርት ቤታቸው ተሰብስበው መጽሐፍቶችን አንብበው እነዚህን መዝሙራት ዘምረው ይለያያሉ፡፡ በዚህም እምነታቸውን ጠብቀው አስጠብቀው እስካሁን ለመኖር
በቅተዋል፡፡
ብዙ አማራጭ ያላቸው በከተሞች የሚኖሩ አንዳንድ ተከራካሪዎች የካሴት
መዝሙራት ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባቸው ዘፈኖች ናቸውና ይላሉ፡፡ ሁሉም ዝማሬ በግዕዝ ብቻ መዘመር አለበት በማለት የማይጨበጥ ክርክርና
ትግል ያስነሳሉ፡፡ ውሃው የእግዚአብሄር ስም ሲጠራበት ጸበል እንደሚሆን የግራሩ ዕጽ በስመ እግዚአብሄር ጽላት እንደሆነ እናምናለን
የሚሉ ሰዎች፤- የእግዚአብሄርን ስም አስተካክሎ የሚጠራና የሚያመሰግን፣ የእመቤታችንን ክብር የሚገልጥ መዝሙር ዘፈን ነው ማለታቸው
አለማመናቸውን ያሳይባቸዋል፡፡ሁሉ በሞላበት ከተማ የሚኖሩ እነዚህ የሞላ የምግብ ብፌ ፊት ቆሞ ይህ ስኳር ያስይዛል ይሄ ደም ግፊት…
እያሉ ምግቡን ሳይመገቡ የሚሳቀቁ ባለጠጎችን ይመስላሉ፡፡በክፍለ ሃገርና በውጭ ሃገር ያሉ ምዕመናን ቃሉን እጅግ ስለተራቡ የካሴቶችን
መውጪያ ቀን በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡የመዝሙራቱን ቃላቶች የህይወታቸው መመሪያ ያደርጓቸዋል፡፡ በየመኪኖቻቸው ግንባር ላይ ይጽፏቸዋል፣
በቤታቸው በመኪናቸው በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ ይጭኗቸዋል፡፡ ስለተጠቀሙባቸውም መዝሞሮቹ ላይ የሚቀርቡትን ቅምጥል አስተያየቶች
መስማት አይፈልጉም፡፡
በከተሞች
ያሉ ጥቂት ሰንበት ትቤቶች ትርጉሙን በሚገባ የማያውቋቸውን የግዕዝ መዝሙራት ብቻ እንዲዘምሩ የሚያደርግ ህግ ቀርጸው ይጠቀማሉ፡፡ይህ
የቤተክርስቲያንን መዝሙራት ጥቅም ያለመገንዘብ ውጤት ነው፡፡ መዝሙር የግዕዝ ቋንቋን የምንጠብቅበት አንዱ መንገድ ቢሆንም የመዝሙር
ዓላማ ግን የግዕዝን ቋንቋን መጠበቂያ ብቻ! ሳይሆን እግዚአብሄርን ማምለኪያ እና ማስተማሪያ መሆኑን መምህራኖቻቸው ማስገንዘብ ይገባቸዋል፡፡ ሌላው በካሴት መዝሙራት ላይ
የሚነሳው ክርክር ዘማሪው ገንዘብ ያገኝባቸዋል የሚል ይሆንና ከባድ ጽንፍ የሚፈጥር ሃሳብ ያመጣል፡፡እርግጥ እነዚህ መዝሙራት በገንዘብ
የሚገዙ ናቸው ምክንያቱም በዘመናዊ የሚዲያ መሳሪዎች ማለትም በሲዲ
እና በካሴት ሲሰሩ ከፍተኛ ወጪ ይወጣባቸዋል፡፡በነጋዴዎችም ስለሚከፋፈሉ የመንግስት ህጋዊ ግብር ይከፈልባቸዋል፡፡ አገልጋዩም የሙሉ
ሰዓት አገልጋይ ስለሆነ ለኑሮው የሚያስፈልገውን ጥቂት ገንዘብ ያገኝባቸዋል፡፡ መጽሐፍም የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ብሎ ይመሰክራል፡፡
የካሴት መዝሙራት የሚያስጨፍሩ ይሆኑ ይሆናል የሚል የሩቅ ፍርሃት የሚያድርባቸው
ሰዎች አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን መዝሙራት ሁለት አይነት ናቸው፡፡ አንደኛው ያለከበሮ የሚዘመረው በበገና ወይ በመሰንቆ
ተጅቦ ቀስ ብሎ የሚፈሰው ዜማ ነው ይህ ብዙ ግዜ በንስሃ ግጥሞች የተሞላ ሲሆን ሰዎች በጸጥታ እንዲያደምጡት ሆኖ የተሰራ ነው፡፡ሁለተኛው
በከበሮ ቁጥጥር ስር የዋለ ዜማ ነው፡፡ ዜማው ግማሹ ክፍል በሽብሸባ ግማሹ ክፍል በከበሮ ድረባ የታጀበ ነው፡፡ይህ በከበሮ ሪትም
ቁጥጥር ስር ስላለ ወዴትም አይነት ስልት ሊንሸራተት አይችልም፡፡መዝሙሩ በዜማው ስልተ ቅርጽ ቢለያይም በአዘማመሩ ግን አንድ አይነት
ወጥ ሆኖ ተቀርጽዋል፡፡ አዘማመሩም የተወሰደው በማህሌት አንድ ወረብ ከተረገጠ በኃላ ሲደረብና ሲሸበሸብ የሚሰጠውን አይነት ስልት
የተከተለ ነው፡፡
መዝሙራቱ ያለባቸውን ተግዳሮት በእግዚአብሄር ቸርነት አልፈው ብዙ ርቀት
ለመጓዝ በቅተዋል፡፡ እግዚአብሄር ቅድመ ቅዱስ ዳዊት ዘማሪዎች ነበሩት፡፡ ነገር ግን አዲሱን የዳዊትን በገና አያስፈልግም አላለም፡፡
ነቢዩ ዳዊትም የዘመራቸው መዝሙራት ይበቁኛል አላለም ለኢትዮጵያ ቅዱስ ያሬድን አስነሳ በዚህም ጌትነቱን አሳየ፡፡በእርግጥ ቅዱስ
ያሬድ በዘመኑ በተነሳ ግዜ ስርዓት አበላሸ ዜማ አበላሸ ያሉ ሰዎች ብዙ ተዋግተውታል፡፡ አስረውም እንደገረፉት በታሪክ ይነገራል፡፡
ነገር ግን ቅዱሱ ዘማሪ እግዚአብሄር አብሮት ስለነበረ እና በአጼ ገብረመስቀል ዘንድ ተቀባይነት ስለነበረው ከሰማይ የተሰጠውን ጸጋ
ለትውልድ ትቶ ሊያልፍ ችሏል፡፡ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ላሉ ዘማሪዎች ትልቅ አስተማሪ ነው በዜማዎቹ ካስተማረው በተጨማሪ ሕይወቱና
ጽናቱ ብዙ ደካሞችን አበርትቷል፡፡ ዛሬም በመዝሙር የተሾሙ ሁሉ አማራጭ ሳያቀርቡ በተለያየ አቅጣጫ ድንጋይ በሚወረውሩ ሳንባላታጣውያን
ሳይደናገጡ ጠንክሮ ቤተክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡በስራዎቻቸው ላይ የሚነሱ ገንቢ ትችቶችን በቅን ልብ መቀበል መዝሙር
የበለጠ የሚጠቅም እንዲሆን ያግዛል፡፡ የባለሞያዎች በጎ እርማት የካሴትን መዝሙራት ጥራት ወደ በለጠ ደረጃ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይቀጥላል
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
ሰባኪ
ሰባኪ
ምስራቹን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ ሥራ የተጠራ ታላቅ አገልጋይ ነው፡፡ ሥራውም ከስራዎች ሁሉ በላይ ነው፡፡ አገልግሎቱም በምርጫ
እና በጸጋ ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ሥራውን ሲሰራም እግዚአብሄርን ወዶ
ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሰባኪ ብዙ አድናቂ፣ ተከታይ፣ ክብርና ገንዘብ ፣በሰው ዘንድ መወደድ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ዋና ዓላው ና
የነፍሱ ጥማት ኢየሱስ ክርስቶስን መውደድ መሆን አለበት፡፡ በጌታ ፍቅር ውስጥ እስከ ስለሌለ በፍቅር የሚሰራ አገልግሎት ጡረታ የለውም፡፡
ሰባኪ በእዚአብሔር ፊት ፤-
ሰባኪው በድካሙ ውስጥ የሚቆጠርለት ዋጋ ከምድር አይደለም፡፡ የትኛውም ክፍያና ክብር የምስክርነትን ደሞዝ የመክፈል አቅም
የለውም፡፡ ትንሽ ዓላማ ያላቸው ሰባኪዎች በዳረጎት ሲጣሉ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የሰባኪው ዋጋ በሰማይ ያለ ነው፡፡ከሰው ፊት በመንፈሱ ጨክኖ ዘወር ማለት አለበት፡፡ ልፋቱም እግዚአብሔር ደስ እንዲለው ብቻ መሆን
አለበት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በሁሉም ቦታ በሁሉም ጊዜ ስላለ በዚህ ዓላማ የተቀረጸ ሰባኪ የሁልጊዜ ትጉህ የሁልጊዜ ሰባኪ
ይሆናል፡፡ልፋቱን ሰው ቢያውቅለት ባያውቅለት ስሜት የማይሰጠው መንፈሰ ብርቱ ይሆናል፡፡ የሰውን ፊት እና ሙገሳ ትቶ በአምላኩ ፊት
የቆመ ሰባኪ እንዴት ተባረከ ይሆን?
ሰባኪ በሰው ፊት - በፍቅር የሆነ ስብከቱ የሰዎችን ድካም ያገናዘበና መፍትሄ
ሰጪ መሆን ይባዋል፡፡ሁል ጊዜ እየራራ መስበክ አለበት፡፡ ሰዎች ሁላችን በጣም ደካማ መሆናችንን በእርግጥ በአምላካችን ፊት ብርቱ
የሆነ ማንም እንደሌለ አምኖ መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህም ለሁሉ አዛኝ፣ ሰውን በስንፍናው እያሳቀቀ የማይፈርድበት ይልቁንም ከድካም
መውጫውን መንገድ በአግባቡ ማሳየት የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡
ጥንቃቄው
ከመጠጥ- መጠጥ
አንድን ሰው ፍጹም የሆነ ነጻነት ይሰጠዋል፡፡የሰከረ ደፍሮ የማይሰራው ኃጢአት የለም፡፡ በጌታ ቃል መጠጥን አብዝቶ በመጠጣት የሚወቀሰው
ሰው አብዝቶ የመጠጣቱን ነገር ከመንፈሳዊው ስፍራ በተለይ ከአገልጋይ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ሰባኪው አንድ ብርጭቆ መጠጥ ሲጠቀም
ሲመለከት ሰነፉ ጠጪ አስር ብርጭቆ አድርጎ ይቀበለዋል፡፡ ስለዚህ ሰባኪው በሰው ፊት ባለመጠንቀቁ ራሳቸውን የማይገዙ እልፍ ሥጋውያንን
ሊያበረታታ ይችላል፡፡
ብዙ መመገብ፤- ብዙ ለምግብ መጎምጀት የጾምን ዓላማ ይቃወማል፡፡ ለሥጋ የተለየ ነጻነት ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ሰባኪው
በማዕድ ፊት ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበረሰቡም በሰው ፊት
መመገብን በጥንቃቄ መያዝ የሚፈልግ ነው፡፡ ርቦት ሳለ አሁን በልቼአለሁ በቃኝ የሚልበት ምክንያት ክብሩን ለመጠበቅ ስለሚፈልግ ነው፡፡
ይሄንን ባህል የተገነዘበው ሰባኪ የተሻለ ጥንቁቅ መሆን ይገባዋል፡፡
መበደር፣- ከሚያስተምረው ሰው ገንዘብ መበደር የሚሰማውን ሰው ልብ ያላላበታል፡፡ አገልጋዩን ተገልጋዩ ዞሮ ዞሮ በእጄ
ነው የሚኖረው እያለው በምን ሞራሉ ሊያስተምረው ይችላል? የስነ ልቦና ምሁራን ተዋሽ፣ ለማኝ፣ ተበዳሪ መሆን የሰውን ክብር ዝቅ
ያደርገዋል ብለው ያምናሉ፡፡መጽሐፍም ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጹዕ ነው ይላል፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔርን በረከት የሚያስተምር
አገልጋይ ከጌታው እጅ ሲበላ መታየት አለበት፡፡የሰውን እጅ ደጅ መጥናት የለበትም፡፡
ጾታ፣- በተቃራኒ ጾታ መጥመድ ላለመያዝ መጠንቀቅ አንዱ የሰባኪው
ሃላፊነት ነው፡፡ከሚያስተምራቸው ምዕመናን መሃከል በፍቅር የተያዘባት ሴት ብትኖር ስሜቱን በቀላሉ መስረቅ ትችላለች፡፡ ስሜት ደግሞ
በሰው ፊት ላይ በቀላሉ ሊነበብ የሚችል ገበና ነው፡፡ ሚዛናዊ እንዳይሆንም ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ከሚያገለግላቸው መሃከል ለሕይወቱ
አጋር መምረጥ ባይከለከልም የሌላውን ሰው አእምሮ የራሱ ጉዳይ ብሎ የሚያልፍ ሰነፍ መሆን አይገባውም፡፡
ባዶ ቃል ኪዳን፤- የማይችለውን ቃል ኪዳን መግባት የለበትም፡፡ እንዲህ አደርግላችኃለሁ
ብሎ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ከሳበ በኃላ ባያደርገው ወይም በዚህ ሰዓት ፕሮግራም እንጀምራለን ብሎ እርሱ በቦታው ባይገኝ በሰሚዎቹ
ዘንድ እንደ ውሸተኛ ሰው ይቆጠራል፡፡
ሃይል- የሰባኪው ትልቁ ጉልበት ከመለኮት የሚሰጠው ሃይል ነው፡፡
ዘወትር በጸሎት መራስ አለበት፡፡ ከመስበኩ በፊት በጌታው ፊት መንበርከክ
አለበት፡፡ ከራሱ የንግግር ችሎታ ከተማረው የስነ መለኮት ትምህርት
ወይም በአጀንዳው ላይ ከአደራጀው ቆየት ያለ ስብከት ይልቅ በእግዚአብሔር ማመኑ እና እርዳታውን መጠየቁ የበለጠ ሃይል
ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡ የሰባኪው ሃይል የአዳማጮቹ ብዛት አይደለም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ፡፡ እርሱ ሳይሆን እሳቱ እንዲሰብክ መፍቀድ አለበት፡፡በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መንፈሱ እንደመሰከረ፤-
መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት እንዲናገር ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ ራዕ 3፤6
እምነት - ሰባኪው በኢየሱስ ክርስቶስ መዳኑን ማመን አለበት፡፡
እኛ ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት አዳነን ያለውን ቅዱስ ጳውሎስ አዋጅ ያመነ መሆን ይገባዋል፡፡ሮሜ 5፤9 ጻድቅ ሰው እግዚአብሔር ባቆመው
የምህረት ኪዳን ማለትም በመስቀል ላይ በተከፈለው ፍጹም ዋጋ እንዲሁ በቸርነቱ በጸጋው መጽደቁን ያምናል፡፡ ለዚህ ነው ጻድቅ በእምነት
ይኖራል ተብሎ የተጻፈው፡፡ እንደዳነ እርግጠኛ ያልሆነ ሰባኪ በምኩራብ ወይም በመስጊዶች ውስጥ እንጂ በተቀደሰችው ቤተክርስቲያን
ፊት ለስብከት መሾም የለበትም፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ምኩራብና የአህዛብ መስኪዶች ሰው ጥሩ ሰው ስለሆነ ነው የሚጸድቀው እንጂ
የተከፈለ ዋጋ የለም ብለው ያምናሉና ነው፡፡ ክርስትና የምስራች ናት ደካሞችን ወደ ምህረቱ የምትጠራ ናት ሰው በሥራው ፍጹም መሆን
ስላልቻለ በእግዚአብሄር ቸርነት/ጸጋ/ ወደ መንግስቱ መጠራቱን ለዚህም ንጹህ ደም መከፈሉን የምትናገር ሃይማኖት ናት፡፡ለዚህም ነው
ቤተክርስቲያን ቅድስት የምትባለው፡፡ በውሃ /በጥምቀት/ የታጠበች በደሙ የተቀደሰች የጸደቀች በመሆኗ ነው፡፡የጥንት መዝሙር እንዲህ
ይላል
የውሃ ግድግዳ የደም መሰረት
ይሄው ከዚህ አለ የኢየሱስ ቤት
ይሄው ከዚህ አለ የአማኑኤል
ቤት
ደግሞም እምነቱ በሌላ አንጻር ጌታ ይረዳኛል፣ ብቻየን አይደለሁም ለአገልግሎት
ለሥራ ስነሳም ይረዳኛል ፣ያሳካልኛል፣ የትኛውም ተራራ በፊቴ ደልዳላ ሜዳ ይሆናል ብሎ ማመን አለበት፡፡ ያለእምነት እግዚአብሔርን
ደስ ማሰኘት አይቻልምና፡፡ ዕብ 11፡6 ይቀጥላል
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
ፍቅር
ፍቅር ፤- ፍቅር የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መቀራረቢያ ሃይል ነው፡፡ይህም ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ ስሜታዊና መንፈሳዊ፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ እብድ ሲሆን ሁለተኛው ሰከን ያለው ነው
እብድ ፍቅር ፤-
የአፍቃሪውን ስሜት ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠራል፡፡የዳዊት ልጅ አምኖን የተያዘው በዚህ አይነት ፍቅር ነበር፡፡ አምኖን ወዳጁ ኢዮናዳብ ከፊቱ የደረሰበትን ጉዳት መለየት እስኪችል ድረስ ስር በሌለው ፍቅር ተጎድቶ ነበር፡፡2ኛ ሳሙ 13 እንዲሁ በዚህ ፍቅር የወደቀ ሰው ምግብ አይበላም መተኛት ይሳነዋል፡፡ካፈቀረው ሰው በስተቀር ለማንም ግድ የለውም፡፡ ወንድ ከሆነ የወደዳት ልጅ ለእርሱ ሙሉ ዓላማው ነች ስለዚህ ከማንም ጋር ስልክ እንድታወራ ወደ ቤተሰቦቿ እንድትሄድ ጓደኞቿን እንድታገኝ አይፈልግም፡፡ ሙሉ ቀን እርሱን ብቻ እንድታሰብ ይፈልጋል፡፡ ሴቷም እንዲሁ፡፡ሲገናኙም አንዳቸው የአንዳቸውን አይን እያዩ ያወራሉ፡፡በአካባቢያቸው እሳት አደጋ እንኳ ቢፈጠር ከሌላ ሰው ዘግይተው ነው የሚነቁት፡፡ስቃይ የተሞላ ደስታ ይደሰታሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወቀሳ ያበዛሉ፡፡ ረስተሸኛል ትተሸኛል ጠልተሸኛል ይላል፡፡ እርሷም እንደሚወዳት ብታውቅም በጣም ከማፍቀሯ የተነሳ ለኔ ግድ የለህም አትወደኝም ….ትናንት የደወለችው ማነች? /ምናልባት ዘመዱ ልትሆን ብትችልም/ የመሳሰለ ጥያቄ ታበዛለች፡፡ አብሯት እየሄደ እያለ ማንንም ቀና ብሎ እንዲያይ አትፈቅድም ሁሌ ጎንበስ ብሎ እንዲራመድ ትፈልጋለች፡፡ ሁለቱም በወቀሳ መፈቀራቸውን እርግጠኛ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ይሄ ፍቅር ስግብግብ ነው ለእኔ ብቻ! ያሰኛል፡፡ እኔን ብቻ እግኚ፣እኔን ብቻ አስብ፣ለኔ ብቻ ደውይ፣ እኔን ብቻ ተመልከት እኔን ብቻ አውሪኝ …ያበዛል፡፡ ለብዙ ወራት በጥንቃቄ በስሜታዊው ፍቅር የቆየ ሰው ያስለመደውን አንድ ቀን ቢያጎድል /ምናልባት ቀኑን ሙሉ ካልደወለ/ ተዓምር የተፈጠረ አድርጎ ያሳያል፡፡ ኩርፊያውና ጥሉ መብረጃ ያጣል፡፡ሌላ ሶስተኛ ሰው እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ልታስታርቋቸው ብትሞክሩ አይ ሞቼ እገኛለሁ ብለው ለገላጋይ ያስቸግራሉ፡፡ አንዳንዴ በተለይ ሴቶቹ ለጓደኞቻቸው አፍቃሪያቸውን ሙልጭ አድርገው ያማሉ ያሳማሉ፡፡ ክፉ ካናገሩ ከ15 ቀን በኃላ አብረው ታገኟችኃላችሁ፡፡ እንደውም ባለፈው እኮ የተጣላን ጊዜ ጓደኛየ ካንተ እንድለያይ መከረችኝ እኔ ግን በጭራሽ አልኩ ብላ ፍቅሯን ታደምቅበታለች፡፡በእውነት
ይህ እብድ ፍቅር ነው፡፡ በብዛት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚከሰት ሲሆን ሰፊ ጊዜ ባላቸውና በሥራ ባልተጠመዱ ሰዎች ቤት በብዛት
ይገኛል፡፡ ስሜታዊው ፍቅር እንደ
እሳት የሚቀጣጠለው
በልብ ወለድ መጽሐፍትና በሙዚቃ ነው፡፡
የትኛውም
ዘፈን
ላፈቀረው
ሰው
ትርጉም
እንዲሰጠው
ያደርጋል፡፡ስለዚህ
ቀኑን
ሙሉ
ዘፈን
ጆሮው
ላይ
አድርጎ
ይውላል፡፡
ይህ ፍቅር ስሜት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ስሜትን ሰድሮ ይይዛል፡፡ ጣፋጭ ወይን ሲጠጡት የሚያሰክር አይመስልም ነገር ግን ከመቀመጫ ሲነሱ እግርን ያብረከርካል፡፡ ይሄ ፍቅር እንደዚህ ነው፡፡ ልብ የሚደነግጥለትን ሰው አትኩሮ በመከታተልና አብዝቶ በማሰብ ፍቅሩ ሊቀጣጠል ይጀምራል፡፡ ይሄ ፍቅር እውር ነው፡፡ በዚህ ፍቅር የተያዘ ሰው በልጅነታችን ዓይናችንን አስረን የምንጫወተውን ያዕቆብ የተባለ ጨዋታ የሚጫወትን ሰው ይመስላል፡፡ አምኖን የአባቱን ልጅ ትዕማርን ያፈቀረው አይኑ ተከፍቶ ይመስላችኃል? 1ኛሳሙ13;2 እብዱ ፍቅር ማየት አይችልም፡፡ ሚስት በቤቱ እያለችው ከስራ ባልደረባው ጋር ቅልጥ ያለ ፍቅር ይይዘዋል፣ ከማያምኑ ሰዎች ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ረስታ በእምነት ከማይመስላት ጋር ልሙትልህ-ፍቅር ይይዛታል፡፡ ትንሹ ልጅ እናቱ ከምትሆን ትምህርት ቤት አስተማሪው ወይም
ከቅርብ ዘመዱ ጋር በአይን ፍቅር ይወድቃል፡፡ ይሄ ፍቅር አይን አለውን? በፍጹም!
ይሄ ፍቅር በደንብ ካልያዙት ጨካኝ ነው፡፡ የሚፈልጋትን ልጅ ያጣ እንደሆነ በራሱ ላይ ጨካኝ ርምጃ ይወስዳል ወይም ልጅቷን ይጎዳል፡፡በስሜታዊ ፍቅር ተይዘው በራሳቸው ዓለም ተጋብተው ልጅ ከመጣ በኃላ አላውቅሽም
ብሎ የሚክደው ጨካኝ ስለሆነ ነው፡፡ ራስ ወዳድም ነው እንደ አምኖን የወደዳትን አታሎ ያጠቃል፡፡1ኛ ሳሙ13;14
በሴት ጓደኞቻቸው ላይ አሲድ የሚደፉ ወጣቶች፣ የሚፈልጉትን አድርገው
የሰውን ህይወት ከጎዱ በኃላ ፊታቸውን የሚያዞሩ የእብዱ ፍቅር ውጤቶች ናቸው፡፡የዚህ ፍቅር እድሜ
የስርቆሽ ካልሆነ ቢበዛ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ምናልባት የስርቆሽ ከሆን ትንሽ ዘመኑ ሊገፋ ይችላል፡፡በዚህ ፍቅር ውስጥ ማስተዋል የሚባለው የመንፈስ ፍሬ አይገኝም፡፡ስለወደዳት ልጅ ክፉ ጎን ለማየት ይቸገራል፡፡ ዋናው ፍቅሩ ነው የሚል ፍልስፍና ይከተላል፡፡የወደድኳት ልጅ ነገ ለህይወቴ አጋር መሆን ትችል ይሆን የሚል ሚዛናዊ እይታ ይጎድለዋል፡፡ ዛሬ ወዷታልና የዘላለም ገነቱ ትመስለዋለች፡፡ ለጸሎት ሲቆም እንኳ ጌታ ሆይ ይህችን ልጅ ፍቃድህ ከሆነ የኔ አድርጋት ፍቃድህ ካልሆነም የኔ አድርጋት ብሎ የጌታን ፍቃድ ሳይሆን የራሱን ፍቃድ ይለምናል፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቃድ ባለማስተዋሉ ሞኝ ሆኗል፡፡ኤፌ5፤17
Subscribe to:
Posts (Atom)