Showing posts with label አግልግሎት. Show all posts
Showing posts with label አግልግሎት. Show all posts
Tuesday, July 8, 2014
ሰላም ለሁላችሁ፤- አገልግሎት ፍላጎት ነው ወይስ ቅባት?
ሰላም ለሁላችሁ፤- አገልግሎት ፍላጎት ነው ወይስ ቅባት?
ዛሬ ብዙ ሰው መናገር ስለሚቻል ሰባኪ እንደሚኮን ትንሽ የማይሻክር ድምጽ ካለ መዘመር እንደሚቻል የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ አርቲስቱና ዘፋኙ በትርፍ ሰዓቱ ዘማሪ ነው፡፡ በክብረ በዓላት ቀን ደግሞ ቅልጥ ያለ ጨፋሪ ሆኖ ይቆማል፡፡ በትርፍ ሰዓትሽ ምን ያደስትሻል ተብላ አንዲት አርቲስት በቀደም እሁድ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተጠየቀች፡፡ ለስለስ ያለሙዚቃ በተለይ የሚያስጨፍር ከሆነ ምድር አይበቃኝም አለች፡፡ ይህችው ሴት ለቤተክርስቲያን መርጂያ መዝሙር ዘምራ/ ለቤተክርስቲያ ያረገችውን መልካም ስራ ባደንቅም/ በየቤተክርስቲያኑ መድረክ አትጠፋም፡፡ አንዳንዴም ቤተክርስቲያን ተደፈረች ድረሱ የሚል ሃሳብ ወለድ ድራማዎችን እየሰሩ የእነሱ መቅደስ /ሰውነታቸው/ ዓለምን የሚያገለግልና ውሳኔአቸውም ለእግዚአብሔር ያልተሰጠ ሆኖ ይታያል፡፡ አንዱ አርቲስት ቀደም ብሎ ጥሩ የሚባል ዝማሬ ሰራ፡፡ ቆየት ብሎ በአንድ መጽሔት እኔ ዘማሪ መሆን አልፈልግም ቤተክርስቲያንን ለመርዳት ነው! ብሎ ቃለምልልስ ሰጠ፡፡ እግዚአብሔር ጉሮሮ ሳይሆን ልብ ነበር የሚያስፈልው፡፡ የሚቃጠል መስዋት ደስ አያሰኝህም የእግዚአብሔር መስዋት የተሰበረ ልብ ነው፡፡ መዝ50፡17 አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የተቀቡ ለዚህ አገልግሎት ራሳቸውን የሰጡትን ዘማሪያንን አይናችሁ ላፈር ብለው እኒሁ የሁለት ቤት ሰዎችን ልዩ አገልጋያቸው አድርገው ይሰይማሉ፡፡ ማንም ሰው ለጌታው ክብር ሊሰጥ እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አውደ ምህረቱና መቅደሱ እግዚአብሔር በጸጋው ቅባት በለያቸው ሰዎች ነው መገልገል ያለበት፡፡ የእግዚአብሔር የሆነ ልዩ ነገር ከሌለ ቅድስና እንዴት ይለያል? የተነሳ ሁሉ ነፍሱን ለጌታው ብቻ ወስኖ ሳይሰጥ ላገልግል ካለ ዓለማዊነት ሰተት ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ይገባል፡፡ቤተክርስቲያ የምትጠፋበት ዋናው መንገድ ዓለማዊነት መንፈሳዊ ለምድ ለብሶ ሲገባባት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ዘፋኞች በድምጻቸው ብቻ ዘማሪዎች ነበሩና ትንሽ ከፍ ሲሉ የተደቁ ዘፋኞች ወደ መሆን ይቀየራሉ፡፡ እድገቱ ከዘማሪነተት ወደ ዘፋኝነት የሆነ ይመስል ያኔ የሰንበት ተማሪ ዲያቆን ነበርኩ ይሉናል፡፡ ማንም ይህን ሆኖ ከሆነ ዘፋኝ የሆነው እንዲህ ብሎ በመናገሩ ማፈር አለበት፡፡ እግዚአብሔር በቂ እንጀራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ እርሱ የዚህ ዓለም ጥበብ የማይደግፈው ራሱን የቻለ ብልጥግና ነው፡፡ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚመጣው ጌታን ሊያግዝ ሳይሆን ራሱን ሰው አድርጎ ሊሰራ ነው፡፡ ፈርቶ፣ ትሁት ሆኖ፣ ለመናገር ሳይቸኩል ደግሞም በእምነት አድጎ ዓለሙን ርግፍ አድርጎ ሊኖር መሆን አለበት፡፡ አገልግሎትም በቅባት እና በመጠራት እንጂ በታለንት ወይ በችሎታ አይደለም፡፡ በመንፈሴ እንጂ በሐይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ዘካ 4፤6 ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና፡፡ ያዕ 3፤1
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
Tuesday, May 27, 2014
ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/
ከቤተክርስቲያን ውጪ ትምህርት?......./ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም/
ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ህዝብ ተከተሉት ማቴ 8፤1 ይህ ምንባብ ጌታ በተራራ ካስተማረ በኋላ ተራራ መውጣት ያቃታቸውን ብዙ ህዝብ ከተራራው በታች እንዳገኘ ይገልጣል፡፡ የልዕልናና የክብር ከፍታ ባለቤት ነችና ተራራ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ሆኖም አማኞች ሁሉ አንድ ሳይቀሩ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የጸጋውን ሚስጢራት የሚካፈሉ አይደለም፡፡ ከተለያየ ድካማቸው ጋር ዓለም ላይ ከግርጌ እንደተበተኑ አሉ፡፡
ቤተክርስቲያን አሁን ባለችበት ሁኔታ ልጆቿን ማስተማር ያለባት በቤተክርስቲያን ቅጥር ብቻ ነው የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ሃሳባቸውን አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመረምር አስተሳሰቡ እጅግ ጠበብ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ሐዋርያት ምኩራብ ቁጭ ብለው ወንበር ዘርግተው ሰብከው ሳይሆን ሄደው ወጥተው ፣ ሮጠው ወድቀው ተነስተው ነው፡፡ የባህር ሞገድ እየመታቸው መርከባቸው እየተሰበረ፣ ከአውሬ ጋር እየታገሉ ከሮም እስከ እስፔን ከእስያ እስከ አፍሪካ ተሰደው ነው፡፡በዘመኑ እግር ያላት ቤተክርስቲያን ነበረችና ከሮማውያን ርኩሰትና ከግሪክ ፍልስፍና የእግዚአብሔርን በጎች ነጥቃ ወደ ሰማያዊ ጥሪ አድርሳለች፡፡ ቀድሞም የቤተክርስቲያን ራስ እና አስተዳዳሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ ብሉ አዟል፡፡ሂዱ የሚለው ትዕዛዝ ተቀምጣችሁ ጠብቁ ከሚል ሃሳብ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ማቴ28፤19
ወንጌል መሰበክ ያለበት ወዳጆቼ እንደሚያምኑበት በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት መሆኑ ዋንኛ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ያልመጣውስ? ካለማወቅ የተነሳ ሃይማኖት ዝም ብሎ ማህበራዊ ልማድ ብቻ ነው ብሎ የቆመውስ? በዓለም ወለድ ፍልስፍና ታስሮ የመስቀሉን ቃል ሳይሰማ በሥጋ የሚኖረውስ? በየዋህነቱ ብቻ ኖሮ ለበላተኞች ራት ለመሆን ጫፍ የደረሰው? ይህን ሁሉ ደካማ መንጋ ማነው የሚያተርፈው? ወንጌል ለቆራቢው ስብከት ቤተክርስቲያን ለሚተጋው ምዕመን ብቻ ከሆነ ሸክም የከበደበት ደካማው ዕጣው ምንድነው? ያላመኑስ እንዴት ወንጌል ሊሰሙ ይችላሉ? ስለዚህ ወንጌልን በሁለቱም መንገድ በተደራጀ ሁኔታ ልናዘጋጅላቸው ተገብቷል፡፡
1- ቤተክርስቲያን መምጣት ለቻሉ፡- ቤተክርስቲያን የመጡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ወንጌላችን ልትረዳቸው ይገባል፡፡ በየክብረ በዓላቱ በወርና በዓመት አባቶቻችን በሰሩት ቅዱስ ስርዓት መሰረት ሰዎች ያለምንም ቀስቃሽ ወደ ቤተክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ እነዚህ መንጎች በተሰናዳ ወንበር በተረጋጋ መንፈስ እነሱ ባሉበት ደረጃ ህይወታቸውን ከአምላካቸው ጋር ሊያጣብቅ የሚያስችል ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዝናብ ቢመጣ ያለምንም ክፍያ የሚሰበሰቡበት ንጹህ አዳራሽ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምክር አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸው የተለዩ ክፍሎች ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከንስሃ አባቶቻቸው ጋር ሚስጢራቸውን የሚያወሩባቸው ከለል ያሉ ቦታዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕጻናቶቻቸው አማርኛ ወይ ሌላ ሃገር በቀል ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሆኑ እንዲሁም በከተሞች የሚኖሩ ከሆነ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እንዲሁም አዲሱን አማርኛ የሚናገሩ መምህራን እንዲያገኗቸው ልዩ መርሃ ግብር/እንደቦሌ መድሐኒዓለም/ ሊዘጋጅላቸው ይገባል፡፡ ከተገኙም አለቆች እና የአውደ ምህረት ገምጋሚዎች እንዲደነቁ ተብሎ ሳይሆን ህዝቡ በሚገባ እንዲገባው እና እንዲመሰረት ማድረግ የሚችል ትምህርት በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት/ጥናት/ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ በቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን አንድ በአንድ ምዕራፍ በምዕራፍ ማስተማር ከጀመርን በጎቹ ከውጭ በሚሰሙት አዲስ ስብከት አይደነቁም፡፡ በቤታችን ሰምተነዋል እናውቀዋለን ብለው ጸንተው ይቆማሉ፡፡እንዲሁም ልዩነትን የሚጸየፉ አንድ አይነት መንፈሳዊነት ያላቸው ያደርጋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን አንድ ዓይነት በማድረግ የተለየ መጽሐፍ ነው፡፡ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ቁንጽል ጥቅስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎቻቸውን አደላድለው እንዲያውቁ ማድረግ እንችላለን፡፡ሌላውን ለመርታትና ለማሳመን ብቻ ሳይሆን ራሳቸው እንዲያምኑ አድርጎ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
2- ከቤተክርስቲያን ውጪ፤- ከቅጥሩ ውጪ ያለው ህዝብ ብዙ ነው፡፡ በምክንያት የታሰረ፣ አውቃለሁ የሚል፣ በዓለም እና በአጋንንት አሰራር የተያዘ፣ እንዲሁ ተፈጥሮአዊ ሰው የሆነ፣ ያላመነ ያልተጠመቀ…….. እጅግ ብዙ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን አስተምራ አምና የመረቀቻቸው፣ ክህነት ድቁናና ቅስና የሰጠቻቸው፣ በጸጋ እግዚአብሔር ሰባኪ ሆነው የተለዩ ስብከቶቻቸውን የአውደ ምህረት ብቻ አድርገው ሊያዘጋጁ አይገባም፡፡ በለቅሶ ቤት፣ ሰርግ ቤት፣ ምዕመናን ቤት/ቤተሰባዊ ጉባኤ/፣ እንደ ፊሊጶስ /በሰረገላ /መጓጓዣ ውስጥ፣ ሴተኛ አዳሪዎች በሚሰበሰቡባቸው ቤቶቻቸው፣ ሰራተኞች ስራ ፍለጋ በጠዋት በሚኮለኮሉባቸው አደባባዮች፡፡ ሊስትሮ እያስጠረጉ ለሊስትሮዎች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ ለገበሬው በእርሻ ስፍራው በጽዋ ማህበራት፣ በሆስፒታል ይህን በመሰለ ቦታ የመዳን ወንጌል እንዲሰሙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጌታ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር እንደዚህ ነው የሰበከው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሐይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህን ኢየሱስን ተመልከቱ ብሎናል፡፡ዕብ 3፤1 በዚህ መንገድ ካልሰራን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤተክርስቲያን እንደ አውሮፓውያን አብያተክርስቲያናት የአረጋውያን ብቻ መሰብሰቢያ ልትሆን ትችላለች፡፡ መሪዎቿና ልጆቻቸው በቋንቋ እና በመረዳት/understanding/ የማይግባቡ በመካከላቸው ያለው ድልድይ የሰፋ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ቤተክርስቲያንም ይህን ተልዕኮ እየተቆጣጠረች ልትመራ ይገባታል፡፡ በዚህ መንገድ የስህተት ትምህርታቸውን በማስተማር ከመንጋው ለይተው ሜዳ የሚጥሉ ሰነፎች በዓለም በብዛት አሉና፡፡ በውጭ ያሉትን ካስተማሩ በኋላ ወደ በረቱ ማስገባት ግዴታ ነው፡፡ ሰብዓ ሰገልን የመራው ኮከብ ቤተልሔም አድርሷቸው እንደተሰወረ አገልግሎታችን በጎቹን አምጥቶ ለሞተላቸው ጌታ በቤቱ ማስረከብ አለበት፡፡ማቴ 2፤9 ምክንያቱም ጸጋው የሚገኝባቸው ሚስጢራት ማለትም ጥምቀት ቅዱስ ቁርባን ተክሊል ወ.ዘ.ተ በውጭ የማይፈጸሙ ናቸውና፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከውጭ የሚገቡት ውስጥ ከሚጠብቋቸው ምዕመናን ጋር መንፈሳዊ ህብረት መፍጠር አለባቸውና ነው፡፡ህብረቱ እስከ ጽዮን ተራራ እስከ ሰማይ የሚደርስ ነው፡፡ ይቆየን፡፡ዕብ 12፤22 ጌታ ሆይ ጉልበታችንን አበርታ
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
Tuesday, August 27, 2013
ሰባኪ ክፍል ሁለት
ሰባኪ ክፍል ሁለት
ጥንካሬ
-ሰባኪ በሁሉም መንገድ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ በአገልግሎቱ የበዛ ከንቱ ውዳሴ ይፈስልታል፡፡ እርሱን በትህትና ሲቋቋም ከንቱ
ክስ ይደርስበታል፡፡ ሰይጣን ይህን የሚያደርገው ስለራሱ እያወራ ራሱን ሲከላከል በትዕቢት እንዲያዝ ነው፡፡ በእነዚህ በሁለቱም ጠንካራ
መሆን አለበት፡፡ ደግሞም ከዓለም የሚመጣው ክብርና ገንዘብ ሃሳቡን ወደ ሌላ ሊመልስበት ስለሚችል በዛም ብርቱ መሆን አለበት፡፡
እርሱ የእግዚአብሔር ስለሆነ የቤት ኪራይ ሃምሳ ብር አይሆንለትም ኑሮውን እንደ አለሙ በጋራ የሚጋፈጠው ነው፡፡ማን ኛውም ሰው የሚደርስበትን
መከራ ሰው እንደመሆኑ ተካፋይ ነው፡፡ ወለጋ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰባኪ በዓለም ላይ እናቱ ብቻ ነበሩ ዘመዱ፡፡ በየለቅሶው ቤት
እየሄደ ለሃዘንተኞች የመጽናናት ትምህርት ይሰጣል፡፡ አንድ ቀን ግን እርሱ ለአገልግሎት ወደ ወረዳ በሄደበት እናቱ ሞተዋል ተብሎ
ተጠራ፡፡ራሱን ሊቆጣጠር አልቻለም፡፡ በአስተማረው ህዝብ ፊት ትዝብት ውስጥ እስኪወድቅ አዘነ፡፡ ከተረጋጋ በኋላ ምነው ቢሉት፡ እግዚአብሔርን
በጣም ስለምወደው በእኔ ላይ ሃዘን የሚያመጣ አልመሰለኝም ነበር፡፡ እናቴንም አብዝቼ ስለምወዳት የምትሞት አልመሰለኝም ነበር፡፡
አሁን ግን ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ ምንም ስሙን ባገለግል ሰው መሆኔን፣ የሰው ሁሉ ፈተናና ትግል የሚጠብቀኝ መሆኔን ተቀንያብሁ አለ፡፡
ንባብ ፤- የሚያነበው የሌለው ሰባኪ የሚሰብከው
የለውም፡፡ ዓለማዊ ዕውቀት በየቀኑ እንደሚሻሻል ሁሉ መንፈሳዊም ዕውቀት ማደግ አለበት፡፡ ምዕመናን አንዳንድ ጊዜ በራሳቸው ጥረት
ብዙ ወደ ላይ እያደጉ ይሆናል ሰባኪው ከእነሱ አንሶ መታየት የለበትም፡፡ ዘመናዊውም ዓለም ወደ ፊት በሄደ ቁጥር የአማኞች ስነልቦና
በዛው መጠን ይሰቀላል፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ይህን ሚዛን ጠብቆ ሁሉን የሚረታ አገልግሎት እንዲኖረው ሕይወቱንና መጽሐፍትን አብዝቶ
ማንበብ ይኖርበታል፡፡ ዋናው መግቦቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት ካልሆነ የልብ ወለድ ሃሳብና ለአሮጊቶች ተረት አገልጋይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች ቅዱሳት/አዋልድ/ መጽሐፍትን
ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ጋዜጦችን መጽሔቶችን ሚዲያዎችን በጥንቃቄ ማየት አለበት፡፡ በስነ ልቦና በጾታና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ
መጽሐፍት መንፈሳዊ ከሆኑት ጋር መነበብ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በአብዛኛው ዶግማ ነክ ጽሑፎችን መጻፍ ይቀናቸዋል ፡፡የግብጽ
አባቶች ደግሞ መንፈሳዊነት ላይ በጥልቀት ይጽፋሉ፡፡ እነዚህንም ማንበብ ለዛ ያለው ሰባኪ ለመሆን ይረዳል፡፡ ለእውቀት እና ለግንዛቤ
የሌላ እምነት ተከታዮችን ጽሁፎች ማንበብ ቢኖረበት ማንነቱን እንዳይቀሙት መጠንቀቅ አለበት፡፡ በተለይ የፕሮቴስታንት ጽሁፎች ማንነትን
የማጣጣል መንፈሳዊው ባህል ላይ የመቀለድ ጸባይ ስላለባቸው የሰባኪው ስነልቦና ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ማንነት ከጠፋ በኋላ ልመልሰው
ቢሉት ብዙ ጉዳት ካላመጣ እሺ አይልም፡፡
ስሜት
- ሰባኪ ሰው ነው፡፡ የትኛውም ሰው የሚሰማው ደስታ፣ ሃዘን፣ ድብርት፣ ብቸኝነት፣ ራሰን መጥላት፣ መሰልቸት፣ ተስፋ መቁረጥ የመሳሰለው
ስሜት ይፈራረቅበታል፡፡ ይህ ስሜት በአገልግሎቱ እንዳይገለጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ተስፋ ቆርጦ ከሆነ ሰው እኮ ዋጋ የለውም ብሎ ቢያስተምር የእግዚአብሔርን ሃሳብ ይቃወማል፡፡እርሱ
ቆጡ ከሆነ ጌታ ቀሳፊ ነው ሊለን አይገባም፡፡ ሁልጊዜ ከራስ ስሜት ተነስቶ ማስተማር፣ መምከር፣ ድምዳሜ ላይ መድረስ ብዙ ጉዳት
ያስከትላል፡፡አዲስ አበባ ውስጥ አንድ አገልጋይ አውቃለሁ በጣም ስሜታዊ ነው፡፡ ሁል ጊዜ ሽብር መስበክ ይወዳል፡፡ችግር ሊፈጠር ነው፣ ጉድ ሊፈላ ነው፣ እሳት ሊነድ ነው ወዘተ……ማለት ይወዳል፡፡
ለመስበክም ለመዘመርም ይሞክራልና ሲሰብክ መርዶ ነጋሪ ይመስላል፡፡ ምዕመናን ተጠንቀቁ እንዲህ ሊሆን ቀርቧል! አዲስ
አበባ ልትበጠበጥ ነው! ጸልዩ! የመሳሰሉ አስደንጋጭ ሃሳብ ወለድ ቃላትን ይናገራል፡፡ምእመናንም ይሄ ምንድነው; ሃገር ሰላም አይደለም እንዴ; ብለው እስኪጠይቁ ድረስ ያሸብራቸዋል፡፡ ነገር ግን የተበጠበጠው የራሱ ስሜትና ሃሳብ
ነበር፡፡ ይሄ ጎጂ ስሜታዊነት ነው፡፡ ሰባኪው መጥፎ ስሜት ሲሰማው ዝም ማለት አለበት፡፡የራሱን ፍርሃት ለሰው ማጋባት የለበትም፡፡
በረከት
- የአገልጋይ መጋቢው አሳዳሪው እግዚአብሔር ነው፡፡ በኪዳኑ ነው የሚያኖረው፡፡ ከልቡ ካገለገለ ዋጋውን ይረሳበት ዘንድ እግዚአብሔር
አመጸኛ አይደለም፡፡
ማን ቀረ በሜዳ ማን ቀረ
በዱር
አንተን ብሎ ወጥቶ እግዚአብሔር
እንዳለ ገጣሚው
በየአጥቢያው የሚከፈለው ደሞዝ ትንሽ ጉርሻ ነው እንጂ ዋናው ደሞዝ በሥላሴ
እጅ ነው ፡፡ ሙሉ ትኩረቱን የእግዚአብሔርን ቤት ለመስራት ካዋለው ጌታ የራሱን ቤት አሳምሮ ይሰራለታል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ አገልጋዩ
በጌታ ሰገነት ላይ የራሱን ቤት የመስራት ዓለማ ብቻ ይዞ ሲደክም ይታይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዳሰበው ሊደላደልለት አይችልም፡፡
መልካሙን አሳዳሪ አምኖ ምንም ሳይቀረው ልፍት ማለት አለበት፡፡ አምላክ በገንዘብ፣ በቤት፣ በልጆች፣ በትዳር፣ አብዝቶ ይባርካል፡፡
ባለ ብዙ ወዳጅም ያደርጋል፡፡ ዓላማን ትቶ የራስን ቤት ለመስራት
መድከም ግን ምናልባት ሙዳይ ምጽዋት ሰባሪ ወይ በሙስና ሥራ ተሳታፊ፣ አታላይ ሰው አድርጎ ሊያበላሽ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ቤትን
ካልሰራ ሰራተኞች በከንቱ ይደክማሉተብሎ ተጽፏል፡፡
ሌላ ዓለም
-በልቡ መናኝና ጎበዝ አገልጋይ የሆነ አንድ ወዳጅ ነበረኝ ለጌታው ሲለፋ አቅም አይቀርለትም፡፡ አንድ ቀን እባክህ ሰይጣን ሌላ
ዓለም እያሳያኝ ነው፡፡ ድካምህ ምንድ ነው እከሌ ዓለምን እያገለገለ ተመችቶት ይኖር የለወይ ይለኛል አለኝ፡፡ በእርግጥ ለአገልጋይ
ጌታ ብቻ ነው ዓለሙ! ሮጦ ያተረፈው በልቡ መቀነት የቋጠረው የወርቅ ገንዘቡ ብዙ የሚገዛበት ውድ መክሊቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ሌላ ዓለም ቢኖር እንኳ የውርደቱ ስፍራ እንጂ የክብሩ አይሆንም፡፡ ጴጥሮስ ጌታን ትቶ እሳት ሲሞቅ መዋረድ የጀመረው በገረዶች ነበረ፡፡
ሰው ማጥመዱን ትቶ ወደ አሳ አስጋሪነቱ በተመለሰም ጊዜ ልፋትና ባዶ መረብ ብቻ ነበር የተረፈው፡፡ዮሐ 21፤3 አገልጋይ ሌላ ዓለም
ፈልጎ ቢንሸራተት መዋረድ የሚጀምረው የተናቁ ባላቸው ተራ መንገዶች ነው፡፡ ጎደለብህ ወደ ፊት ምን ትሆናለህ ዛሬ ካልተማርክ ካልነገድክ
የት ትወድቃለህ; እያለ ጠላት የዓለምን መንጠልጠያዎች ከጌታ ክንድ አስበልጦ ያሳየዋል፡፡ የባልንጀሮቹን
ቤት፣ ዓለምን ያገለገሉ እኩዮቹን ኑሮ እያሳየ ልቡን ይዋጋዋል፡፡እንደ ጌታችን ወደ ታላቅ ተራራ በምኞት ወስዶ ያቆመዋል፤ ወድቀህ
ብትሰግድልኝ/ አገልግሎትህን ብትተውልኝ/ ይህን ዓለም እሰጥሃለሁ ይለዋል፡፡ማቴ 4፤9 ያልበረታ ከሆነ ሞቶ ይቀራል፡፡አገልጋይ ራሱን
ከሌላ ዓለም ውጊያ በጸሎትና በትጋት ሊጠብቅ ይገባል፡፡
ትጋት፡- የእግዚአብሔርን ስራ በቸልታ የሚሰራ የተረገመ ይሁን ይላል መጽሐፍ! በጸሎት
ብዙ መትጋት፣ በመስበክ በመዘመር ብዙ መትጋት፣ በማንበብ በምመከር ብዙ መትጋት፣ በመሞከር በመሞከር ብዙ መትጋት፣ ቤተክርስቲያንን
በማልማት ብዙ መትጋት፣ የካህናቱን ኑሮ ለመቀየር ብዙ መትጋት፣ በሰላሙም በጦርነቱም ሰዓት መትጋት ያስፈልጋል፡፡በተነቀፉም ሰዓት
ፍጥነትን ሳይቀንሱ ብዙ መትጋት፣ በተመሰገኑም ሰዓት ውዳሴን ለማዳመጥ ቆም ሳይሉ ብዙ መትጋት ይገባዋል፡፡
ማዳመጥ
፡- የማገልገል ዕድል ማግኘት ብዙ ማወቅ አይደለም፡፡ የሚያስተምራቸውን ሰዎች በደንብ ማዳመጥ ችግሮቻቸውን ለይቶ ለማወቅ ይረዳዋል፡፡ ከብርታታቸውም ለመማር ያግዛል፡፡ በደንብ ያዳመጠ
ሰው በሚገባ ሊደመጥ ይችላል፡፡ ቶሎ ቶሎ መናገር ያለመማር ወይ ያለመብሰል ምልክት ነው፡፡ ሰነፍ እንኳ ቢሆን ዝም ያለ እንደ አዋቂ
ይቆጠራል ፡፡
ያለስስት፡- አንዳንድ ሊቃውንት ቆሎ ትምህርት ቤት ውሻ ነክሶኝ የተማርኩትን
በቀላሉ አልሰጥም የሚል ስስት ይታይባቸዋል፡፡ አገልጋይ ግን የዛሬ እንጂ የነገ ሰው አይደለምና በሰጠው እድሜ ያለውን፣ የሚያውቀውን
ያለስስት ማስተማር አለበት፡፡እንደ ልባሙ መጋቢ በተሾመበት ገንዘብ ያለስስት አበዳሪ መሆን ይገባዋል፡፡ አንድ ወንድም በታክሲ እየሄደ
የሚያነበውን ስልክ ደውሎ ሲያካፍል ሰምቼአለሁ፡፡ ያወቁትን ለማሳወቅ
መቸኮል እንዴት ደስ ይላል፡፡ ፍቅር እንደቀይ ሽንኩርት ናት ዝም ብላ እየሰጠች ታልቃለች ፡፡አገልጋይ ጉልበቱን ዕውቀቱን ሳይሰስት
ለጌታው ክብር ማዋል አለበት፡፡ብዙ ሰዎች ስላልመጡ ብሎ ከእውቀቱ ቆጥቦ ቢያስተምር ብዙዎች ሲሰበሰቡለት የሚያውቀውን ሁሉ ካልሰበኩ
ቢል የእግዚአብሔርን ሃሳብ ከማገልገል እንደወጣ ሊረዳ ይገባዋል፡፡
ዝግጅት፡- ምንም የሚያስተምረውን እንደሚያውቀው ቢሰማውም ወይ የሚዘምረውን
እንደለመደው ቢያስብ መዘጋጀት ግን አለበት፡፡ ቤታችን ውስጥ ተከድኖ የዋለ ያልሞቀ ምግብ የምንመገበው ሲቸግረን ብቻ ነው ካልሆነ
እሳት ላይ አሙቀን እንመገበዋለን፡፡ አገልጋዩም አገልግሎቱን እሳት
ማስነካት አለበት፡፡ በመሰዊያው ፊት የሚቀርበው አገልግሎት የቀዘቀዘ ሙት መሆን የለበትም፡፡ በዝግጅት የታሸ እና የጣፈጠ እንዲሆን
መጣር አለበት፡፡ ዘማሪው በሄደበት አገልግሎት ሰባኪው ካስተማረው
ትምህርት ጋር የሚሄድ መዝሙር ለመዘመር መዘጋጀት አለበት፡፡ ክርስቶስ ከሞት ተነሳ ብሎ አስተምሮ ዘማሪው የማይሞተው ሞተ ብሎ ማሳረግ
የለበትም፡፡በእለቱ ለሚነረው አገልግሎት ትንሽ ሰዓት መንበርከክ የዝግጅቱ ዋናው አካል ነው፡፡
ጥልን ልዩነትን መጸየፍ ፡- ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አንዳንድ ሰባኪዎች ጥልን በሃይማኖት ስም በቤተክርስቲያን
መድረክ ላይ መስበክ እንደትልቅ አገልግሎት ይቆጥሩታል፡፡ ይሄን በማድረጋቸው ትንሽም አይሰማቸውም፡፡ ቤተክርስቲያን ቅድስና አልባ
እንደትሆን ትልቅ በር የሚከፍትው አንዱ ይሄ መንገድ ነው፡፡ በመቅደሱ የጥፋት ርኩሰት ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል ከተባለው አንዱ
ይሄ ነው፡፡ ሰባኪ ጥልን መጸየፍ አለበት!!
ከእግዚአብሔር ይልቅ በከበቧቸው አድናቂዎቻቸው ሚመኩ ሰዎች ለጥል ቅርብ
ናቸው፡፡አጋዥ አለን እያሉ በእግዚአብሔር ከማመን ዘወር የሚሉ፣ ወይ ለጠባቸው የምዕመናንን ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች አልፎ አልፎ ይታያሉ
የሚሰማቸውን ይናገራሉ የሚያመጣውን ውጤት ምን ይሁን ምን ግድ የላቸውም፡፡ በክርስቶስ አውደ ምህረት ጥልን ማገልገል እጅግ አሳፋሪ
ታሪክ ነው፡፡ ጠብን በህዝብ ፊት አውጆ የወረደ አገልጋይ አገልጋይ ሆኖ ባይጠራ ይሻለው ነበር፡፡ ጥልን መጸየፍ የጌታን መስቀል
መሸከም ነው፡፡በመስቀሉ ሰላም አውርዶ ከመምጣት በቀር ሌላ አገለግሎት ከኛ ይራቅ! በፍጹም ሰው እንዲለያይ ማድረግ ተገቢ አይደለም! በወንድሞች መሃል ልዩነትን
የሚዘራ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተጠላ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በተለይ በአንድ አንድ መነኮሳት ዘንድ/ሕዝቡን አጋጭተው ከሃገር
በሚወጡ/፣ በባህታውያን ዘንድ፣ በአፍቃሪ ማህበራት ዘንድ፣ ትልቅ ሰባኪ ነን ዘማሪ ነን በሚሉ ዘንድ፣ ከእኔ በቀር ሃይማኖተኛ በሚሉት
ትምህርት አልባ ሰዎች ዘንድ ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያንን መዓዛ ያጠፋል፡፡ ይቀጥላል ሼር አድርጉት
Thursday, July 11, 2013
ሰባኪ
ሰባኪ
ምስራቹን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ ሥራ የተጠራ ታላቅ አገልጋይ ነው፡፡ ሥራውም ከስራዎች ሁሉ በላይ ነው፡፡ አገልግሎቱም በምርጫ
እና በጸጋ ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ሥራውን ሲሰራም እግዚአብሄርን ወዶ
ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሰባኪ ብዙ አድናቂ፣ ተከታይ፣ ክብርና ገንዘብ ፣በሰው ዘንድ መወደድ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ዋና ዓላው ና
የነፍሱ ጥማት ኢየሱስ ክርስቶስን መውደድ መሆን አለበት፡፡ በጌታ ፍቅር ውስጥ እስከ ስለሌለ በፍቅር የሚሰራ አገልግሎት ጡረታ የለውም፡፡
ሰባኪ በእዚአብሔር ፊት ፤-
ሰባኪው በድካሙ ውስጥ የሚቆጠርለት ዋጋ ከምድር አይደለም፡፡ የትኛውም ክፍያና ክብር የምስክርነትን ደሞዝ የመክፈል አቅም
የለውም፡፡ ትንሽ ዓላማ ያላቸው ሰባኪዎች በዳረጎት ሲጣሉ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የሰባኪው ዋጋ በሰማይ ያለ ነው፡፡ከሰው ፊት በመንፈሱ ጨክኖ ዘወር ማለት አለበት፡፡ ልፋቱም እግዚአብሔር ደስ እንዲለው ብቻ መሆን
አለበት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በሁሉም ቦታ በሁሉም ጊዜ ስላለ በዚህ ዓላማ የተቀረጸ ሰባኪ የሁልጊዜ ትጉህ የሁልጊዜ ሰባኪ
ይሆናል፡፡ልፋቱን ሰው ቢያውቅለት ባያውቅለት ስሜት የማይሰጠው መንፈሰ ብርቱ ይሆናል፡፡ የሰውን ፊት እና ሙገሳ ትቶ በአምላኩ ፊት
የቆመ ሰባኪ እንዴት ተባረከ ይሆን?
ሰባኪ በሰው ፊት - በፍቅር የሆነ ስብከቱ የሰዎችን ድካም ያገናዘበና መፍትሄ
ሰጪ መሆን ይባዋል፡፡ሁል ጊዜ እየራራ መስበክ አለበት፡፡ ሰዎች ሁላችን በጣም ደካማ መሆናችንን በእርግጥ በአምላካችን ፊት ብርቱ
የሆነ ማንም እንደሌለ አምኖ መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህም ለሁሉ አዛኝ፣ ሰውን በስንፍናው እያሳቀቀ የማይፈርድበት ይልቁንም ከድካም
መውጫውን መንገድ በአግባቡ ማሳየት የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡
ጥንቃቄው
ከመጠጥ- መጠጥ
አንድን ሰው ፍጹም የሆነ ነጻነት ይሰጠዋል፡፡የሰከረ ደፍሮ የማይሰራው ኃጢአት የለም፡፡ በጌታ ቃል መጠጥን አብዝቶ በመጠጣት የሚወቀሰው
ሰው አብዝቶ የመጠጣቱን ነገር ከመንፈሳዊው ስፍራ በተለይ ከአገልጋይ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ሰባኪው አንድ ብርጭቆ መጠጥ ሲጠቀም
ሲመለከት ሰነፉ ጠጪ አስር ብርጭቆ አድርጎ ይቀበለዋል፡፡ ስለዚህ ሰባኪው በሰው ፊት ባለመጠንቀቁ ራሳቸውን የማይገዙ እልፍ ሥጋውያንን
ሊያበረታታ ይችላል፡፡
ብዙ መመገብ፤- ብዙ ለምግብ መጎምጀት የጾምን ዓላማ ይቃወማል፡፡ ለሥጋ የተለየ ነጻነት ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ሰባኪው
በማዕድ ፊት ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበረሰቡም በሰው ፊት
መመገብን በጥንቃቄ መያዝ የሚፈልግ ነው፡፡ ርቦት ሳለ አሁን በልቼአለሁ በቃኝ የሚልበት ምክንያት ክብሩን ለመጠበቅ ስለሚፈልግ ነው፡፡
ይሄንን ባህል የተገነዘበው ሰባኪ የተሻለ ጥንቁቅ መሆን ይገባዋል፡፡
መበደር፣- ከሚያስተምረው ሰው ገንዘብ መበደር የሚሰማውን ሰው ልብ ያላላበታል፡፡ አገልጋዩን ተገልጋዩ ዞሮ ዞሮ በእጄ
ነው የሚኖረው እያለው በምን ሞራሉ ሊያስተምረው ይችላል? የስነ ልቦና ምሁራን ተዋሽ፣ ለማኝ፣ ተበዳሪ መሆን የሰውን ክብር ዝቅ
ያደርገዋል ብለው ያምናሉ፡፡መጽሐፍም ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጹዕ ነው ይላል፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔርን በረከት የሚያስተምር
አገልጋይ ከጌታው እጅ ሲበላ መታየት አለበት፡፡የሰውን እጅ ደጅ መጥናት የለበትም፡፡
ጾታ፣- በተቃራኒ ጾታ መጥመድ ላለመያዝ መጠንቀቅ አንዱ የሰባኪው
ሃላፊነት ነው፡፡ከሚያስተምራቸው ምዕመናን መሃከል በፍቅር የተያዘባት ሴት ብትኖር ስሜቱን በቀላሉ መስረቅ ትችላለች፡፡ ስሜት ደግሞ
በሰው ፊት ላይ በቀላሉ ሊነበብ የሚችል ገበና ነው፡፡ ሚዛናዊ እንዳይሆንም ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ከሚያገለግላቸው መሃከል ለሕይወቱ
አጋር መምረጥ ባይከለከልም የሌላውን ሰው አእምሮ የራሱ ጉዳይ ብሎ የሚያልፍ ሰነፍ መሆን አይገባውም፡፡
ባዶ ቃል ኪዳን፤- የማይችለውን ቃል ኪዳን መግባት የለበትም፡፡ እንዲህ አደርግላችኃለሁ
ብሎ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ከሳበ በኃላ ባያደርገው ወይም በዚህ ሰዓት ፕሮግራም እንጀምራለን ብሎ እርሱ በቦታው ባይገኝ በሰሚዎቹ
ዘንድ እንደ ውሸተኛ ሰው ይቆጠራል፡፡
ሃይል- የሰባኪው ትልቁ ጉልበት ከመለኮት የሚሰጠው ሃይል ነው፡፡
ዘወትር በጸሎት መራስ አለበት፡፡ ከመስበኩ በፊት በጌታው ፊት መንበርከክ
አለበት፡፡ ከራሱ የንግግር ችሎታ ከተማረው የስነ መለኮት ትምህርት
ወይም በአጀንዳው ላይ ከአደራጀው ቆየት ያለ ስብከት ይልቅ በእግዚአብሔር ማመኑ እና እርዳታውን መጠየቁ የበለጠ ሃይል
ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡ የሰባኪው ሃይል የአዳማጮቹ ብዛት አይደለም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ፡፡ እርሱ ሳይሆን እሳቱ እንዲሰብክ መፍቀድ አለበት፡፡በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መንፈሱ እንደመሰከረ፤-
መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት እንዲናገር ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ ራዕ 3፤6
እምነት - ሰባኪው በኢየሱስ ክርስቶስ መዳኑን ማመን አለበት፡፡
እኛ ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት አዳነን ያለውን ቅዱስ ጳውሎስ አዋጅ ያመነ መሆን ይገባዋል፡፡ሮሜ 5፤9 ጻድቅ ሰው እግዚአብሔር ባቆመው
የምህረት ኪዳን ማለትም በመስቀል ላይ በተከፈለው ፍጹም ዋጋ እንዲሁ በቸርነቱ በጸጋው መጽደቁን ያምናል፡፡ ለዚህ ነው ጻድቅ በእምነት
ይኖራል ተብሎ የተጻፈው፡፡ እንደዳነ እርግጠኛ ያልሆነ ሰባኪ በምኩራብ ወይም በመስጊዶች ውስጥ እንጂ በተቀደሰችው ቤተክርስቲያን
ፊት ለስብከት መሾም የለበትም፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ምኩራብና የአህዛብ መስኪዶች ሰው ጥሩ ሰው ስለሆነ ነው የሚጸድቀው እንጂ
የተከፈለ ዋጋ የለም ብለው ያምናሉና ነው፡፡ ክርስትና የምስራች ናት ደካሞችን ወደ ምህረቱ የምትጠራ ናት ሰው በሥራው ፍጹም መሆን
ስላልቻለ በእግዚአብሄር ቸርነት/ጸጋ/ ወደ መንግስቱ መጠራቱን ለዚህም ንጹህ ደም መከፈሉን የምትናገር ሃይማኖት ናት፡፡ለዚህም ነው
ቤተክርስቲያን ቅድስት የምትባለው፡፡ በውሃ /በጥምቀት/ የታጠበች በደሙ የተቀደሰች የጸደቀች በመሆኗ ነው፡፡የጥንት መዝሙር እንዲህ
ይላል
የውሃ ግድግዳ የደም መሰረት
ይሄው ከዚህ አለ የኢየሱስ ቤት
ይሄው ከዚህ አለ የአማኑኤል
ቤት
ደግሞም እምነቱ በሌላ አንጻር ጌታ ይረዳኛል፣ ብቻየን አይደለሁም ለአገልግሎት
ለሥራ ስነሳም ይረዳኛል ፣ያሳካልኛል፣ የትኛውም ተራራ በፊቴ ደልዳላ ሜዳ ይሆናል ብሎ ማመን አለበት፡፡ ያለእምነት እግዚአብሔርን
ደስ ማሰኘት አይቻልምና፡፡ ዕብ 11፡6 ይቀጥላል
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
Wednesday, July 10, 2013
ሰላም ለሁላችሁ
ሰላም ለሁላችሁ፤- እግዚአብሔር
ሰውን የሚረዳው ወይም/underesatand/
የሚያደርገው በምን መጠን
እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ?
ሰው ለእግዚአብሔር ችግሩን
ድካሙን ሲነግረው እርሱ
የሚሰማው ከጀርባው ታሪኩ
ተነስቶ ነው ከአስተዳደጉ፣
ከደረሰበት ማህበራዊ ተጽዕኖ፣
ከስነልቦና ችግሩ፣ ወንጌልን
ካለመማሩ፣ የሰው እርዳታ
ካለማግኘቱ፣ የተጎዳ ከመሆኑ
ከእነዚህ ሁሉ ችግሮቹ
ተነስቶ ይሰማዋል፡፡ ስለዚህም
ጨክኖ አይፈርድበትም ይራራለታል
እንጂ! አብዛኛው ሰው
ብዙውን ጊዜ አንድን
ሰው የሚዳኘው ስለሰውየው
በሰማው ወይ አልፎ
አልፎ ባየው ነገር
ይሆንና ሳይራራ ይወስንበታል፡፡
መጥላት ካለበትም ከዚያ
ቀን ጀምሮ ይጠላዋል
ይሸሸዋል፡፡ ጌታ ግን የተለየ ነው፡፡ ባለችግሩን ከችግሩ ሳያወጣ አይተወውም፡፡ ሰባራውን ጠጋኝ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ እመኑኝ እግዚአብሔር ስለእግዚአብሔር እንደሰማነው አይደለም፡፡ እኛ እንኳ ሰው ስለእኛ እንደሚናገረው አይደለንም እኮ! አምላካችን ግን ምን ያህል መሃሪ፣ ምን ያህል ታጋሽ፣ ምን ያህል ረዳት፣ ምን ያህል ተሸካሚ ፣ ምን ያህል አስፈሪ፣ ምን ያህል ታላቅ፣ ምን ያህል ቅን ደግሞም ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ማን ሊገምት ይችላል? እባካችሁ ኑ እግዚአብሔር ይቀፋችሁ አምላካችሁ ያኑራችሁ ጌታችሁ እንደገና ይስራችሁ፤
Subscribe to:
Posts (Atom)