Showing posts with label ምክር. Show all posts
Showing posts with label ምክር. Show all posts
Wednesday, September 24, 2014
ሰላም ለሁላችሁ፤- መስቀል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል መሰቀሉን የምናስብበት ነው
ሰላም ለሁላችሁ፤- መስቀል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል መሰቀሉን የምናስብበት ነው፡፡ ገላ 3፤13 መሰቀሉ የጌታን አሸናፊነት ያሳየ ነው፡፡ ክርስቶስ ገዳዮችን ብቻ ሳይሆን ሞትን የተዋጋ ነጻ አውጪ ነው፡፡ በመስቀል ሲሞትም እየማረከ ከፍ እያለ ነበር እንጂ እንደ ሰው እያለቀለት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ትግሉን በትንሳኤ ደምድሞታል፡፡ ስለዚህ ሞቱን ክብር ብሎ ጠርቶታል፡፡ ዮሐ 17፤2 መሰቀሉም ወደ ላይ ከፍ ማለቱ ነበር፡፡ ተሰቀለ ከፍ ከፍ አለ ማለት ነው፡፡..እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እሰበስባለሁ..ዮሐ 12፤32 እንዳለ፡፡ እኛም በመሰቀሉ ወደ ላይ ክፍ ብለናል፡፡ ወደ ፊት ወደ እርሱ ለመነጠቅ ከበጉ ሰርግ ለመታደም በተስፋ የምንጠብቅበትን መግባት አግኝተናል፡፡ ምልክቱ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነው … ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ሆኖ ተሹሟል…ሉቃ 2፤35 መስቀሉም በጉ የተሰዋበት ቅዱስ መሰዊያ ነው፡፡ ያዳኛችንን ቅዱስ ሞት የምናስብበት ነው፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ፡፡
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት www.ashenafigmariam.blogspot.com
Friday, September 19, 2014
ሰላም ለሁላችሁ፤- ምህረቱ ለሚፈሩት እስከ ትውልድ ትውልድ ነው…ሉቃ 1፤50 በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ሆይ፤- እግዚአብሔርን በፍቅር መፍራት ስለእርሱ ከማወቅ ይጀምራል፡፡ ጌታችሁን የምታውቁት ስለርሱ ፍላጎትና ፍለጋ ሲኖራችሁ ነው፡፡ በርግጥ አሁን ያላችሁበት ኑሮ የማንንም እርዳታ የማይፈልግ ይሆናል፡፡ ጊዜአችሁን ምቾታችሁን ሊያስጠብቅላችሁ ይችላል በምትሉት ነገር ብታጠፉ ደስ ይላችኋል፡፡ ነገር ግን እናንተ የዛሬው ሰዎች ብቻ አይደላችሁም የምድርም ኑሮ ብቻ አይደለም ያላችሁ፡፡ትውልዳችሁን የሚረከብ ጌታ አለ፡፡ ዘላለም የሚባል ዓለም አለ፡፡ ወደዛ የምትደርሱበት መንገድ ጌታ ነው ፡፡ ለትውልዳችሁ የምታወርሱት ከምድር የሆነ ጌጠኛ ድንጋይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንደ አብርሃም የዘላለም ምህረት የመለኮት ጥበቃ ለልጆቻችሁ ማቆየት አለባችሁ፡፡ ይህን የምታገኙት ልዑሉን ስታውቁትና ስትፈሩት ነው፡፡ ለትውልዳቸው ርግማን ትተው ያለፉ የትናንት ሰዎች ነበሩ፡፡ የሰው ደም በከንቱ ያፈሰሱ፣ በድሃ እንባ የታጠቡ፣ ሃገር ያፈረሱ፣ ልዑሉን የረገሙ፣ ማምለኪያውን ያቃጠሉ፣ በጉቦ የፈረዱ፣ ባይተዋሩን ፊት የነሱ… እነዚህ መርገምን ለትውልዳቸው ትተው ሄደዋል፡፡ የፈሩት ግን ተመርቀዋል ከነልጆቻቸው ምህረትን ጠግበዋል፡፡የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ምሳ 1፤7 ተባረኩ፡፡
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት visit www.ashenafigmariam.blogspot.com
Wednesday, April 30, 2014
የምትወዱአቸውን ግደሏቸው
የምትወዱአቸውን ግደሏቸው
ጌታ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ልባችንን አስፍቶ ነው፡፡ እንውደድ ካልን ብዙ ሰዎችን እንወዳለን፡፡ የሰውን ህይወት ከሚገዙ ሁለት ነገሮች አንዱ ፍቅር ነው፡፡ ህግም እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ሃይልህም በፍጹም ሃሳብህ ውደድ እና ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ በሚሉ ሁለት ትዕዛዞች ተጠቅልሏል፡፡ሉቃ 10፤27 ስለዚህ የሰው ነፍስ በሁለት ፍቅሮች መካከል ትኖራለች፡፡ እግዚአብሔርን የምንወድበት ፍቅር በፍጹም ነፍስ፣ ሃይል፣ ልብ እና ሃሳብ ነው፡፡ ይሄ ፍቅር በተፈቃሪው/በጌታ/ ላይ ይታመናል ተስፋ ያደርጋል ምንጊዜም የማይጥል እንደሆነ አስቦ ይደገፍበታል፡፡ከራስ በላይ ይወዳል ምናልባት ምቾትን ጥሎም ቢሆን ቅር አይለውም፡፡ ጌታም እንዲህ ከወደዱት አይጥልም፡፡ ፍቅሩም ለዘላለም ነው፡፡ አለኝ ቢሉት ይኖራል እርሱ ያውቃል ቢሉት ያውቃል፡፡ ቢወራረዱበት ይረታል፡፡ እወቁልኝ ቢሉት አያሳፍርም፡፡ ሰውን ግን በዚህ አይነት መንገድ መውደድ ጉዳት ያመጣል፡፡ ያልታዘዘም መንገድ ነው፡፡ ሰው የሚወደደው እንደራስ ነው፡፡ ለሰው የምታደርጉትን ነገር ከራሳችሁ አንጻር እስቲ እዩት፡፡ ትንሽ ልጅ ተርቦ ብታዩ በልባቸችሁ የኔ ልጅ ቢሆንስ ስትሉ የበለጠ ትራራላችሁ፡፡ የሰው ኃጢያት ተገልጦ በአደባባይ ሲዋረድ ብታዩ እኔ ብሆንስ ስትሉ እጅግ ታዝናላችሁ፡፡እኔ እንደምሞት እርሱም እኮ እንዲሁ ነው ትላላችሁ፡፡ እንደራስ መውደድ እንዲህ ነው፡፡
አንዳንድ ግዜ ግን ሰው ሰውን በፍጹም ነፍስ በፍጹም ልብ በፍጹም ሃሳብ በፍጹም ሃይል መውደድ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ተስፋ መመኪያ ያደርገዋል፡፡የማይሳሳት ፍጹም አድርጎ ያስበዋል፡፡ ስህተቱን በሚያዩ ሰዎች ላይ ቂም ይይዛል፡፡ ያለእርሱ መኖር አልችልም ብሎ ያብዳል፡፡ የሞተ እንደሆነ ገመድ አቀብሉኝ እንዴት እኖራለሁ ወይ አብሬ እቀበራለሁ ተውኝ ብሎ ለያዥ ያስቸግራል፡፡ እርሱ ከተቀየመ ሰማይ የተደፋበት ያክል ተስፋ ቢስ ይሆናል፡፡ አንድም ቀን ይሞታል ብሎ አያስብም፡፡ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ጋር አመሳስሎ የማይወድቅ ትምክት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡እርሱ ካለኝ ምን ሆናለሁ ይላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ከሚጸልይባቸው ደቂቃዎች ይልቅ ለዚህ ሰው ችግሩን የሚነግርባቸው ሰዓቶች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ቤቱን በሰው አጥንት ግድግዳውን በሰው ሥጋ ያጠረ ሰውን ይመስላል፡፡አቤት ይሄ ሰው ውድቀቱ! ይህ ሰው ልቡ የተሰበረ እለት ለመጠገን በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ትምክህቱን ሲነጠቅ መኖሩም አብሮ ይጠፋል፡፡ እርሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ሳለ ራሱን እንደ ማይጠቅም አድርጎ ይቆጥራል ለከፍተኛ የስነልቦና ችግር ይጋለጣል፡፡
እባካችሁ የምትወዷቸውን ሰዎች በአእምሮአችሁ ግደሏቸው፡፡ አናቴ ብትሞት? አባቴ ቢሞትስ ?ፍቅረኛዬ ወይ ሚስቴ ወይ ባለቤቴ ቢሞትስ ? ልጄ ቢሞትስ? ያ ችግር ሲገጥመኝ እየተሯሯጠ የሚያግዘኝ ባለስልጣን ወዳጄ ቢሞትስ? እኔ ካለሁ አይዞህ ያለኝ አጎቴ ድንገት ቢያንቀላፋስ……. መኖር እችላለሁ? በሉ እስቲ! ጌታ ለተከታዮች እንደሚሞትና በሶስተኛው ቀን እንደሚነሳ ይነግራቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን አላስተዋሉም፡፡ ሁሌ መኖር ያለ ይመስላቸው ነበር፡፡ማር 9፤9
ጌታችን አስቀድሞ በወዳጆቹ አእምሮ ሞቱን አትሞ ነበር፡፡ የምትወደዱ ሰዎችም አንድ ቀን እንደማትኖሩ ለሚወዷችሁ ንገሩ፡፤ ዝም ብላችሁ አትኑሩ፡፡ ለህጻናት ልጆቻችሁ እንኳ እኔ አንድ ቀን እሞታለሁ የማይሞተው አምላክ አሳዳሪ በሰማይ አለላችሁ እንዳትፈሩ በሏቸው፡፡ አለሁ እያላችሁ እንዳታልሏቸው፡፡
የአብ ጸጋ የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቃችሁ
Friday, March 28, 2014
battery low- ሃይል አለቀ የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡
battery low- ሃይል አለቀ
የእጅ ስልካችን ቀን ከተጠቀምንበት በኋላ ማታ ሃይል አለቀ/ battery low/ ይለናል፡፡ እኛም ከሃይል ጋር አገናኝተን እንሞላዋለን፡፡ ነፍሳችንም እንደዚህ ስልክ ነች፡፡ ትደክማለች፡፡ ከሃይሏ ከተለያየች battery low ትላለች፡፡በጋለ ፍላጎት እናመልክ ከነበረ መንፈሳችን ሙትት ይልብናል፡፡ መጸለይ አሰልቺ ሥራ ይሆንብናል፡፡ ቃል ወደምንሰማበት ጉባኤ ለመሄድ ፍላጎት ስለምናጣ አገልግሎቱን እንተቻለን፡፡ ምን እነሱ ሰዓት አያሳጥሩ! የሚሰብኩት በግዕዝ ነው አይገባ! ወ.ዘ.ተ. ቅያሜ ለበስ ንግግሮች እናበዛለን፡፡ ይሄኔ ነፍሳችን battery low እያለችን ነው፡፡ ጓደኞቻችን ስለፓለቲካ፣ ስለኳስ ፣ ስለጌጣጌጥ የሚያወሩ ብቻ ቢሆን ደስ ካለን፣ መንፈሳዊ ሃሳብ ካላቸው ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ ከወደድን ሃይላችን እያለቀ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ያነበብናቸው መጽሐፍት ፍልስፍናና ልብወለድ ብቻ ከሆነ ብዙ ጊዜያችንን ሙዚቃ በማዳመጥ ካሳለፍን ድሮ የነበረን የሞቀ ልባችን ከቀዘቀዘ battery low እያለን ነው፡፡ ወንጌልን በመረዳት ስም ከተግባራዊ አምልኮ ማለትም ለብርቱ ጾም፣ ከጸሎት፣ ድሆችን ከመጎብኘት፣የተቀቡትን ከማክበር ፣ ንስሃ ገብቶ በራስ ስንፍና ከመጸጸት ይልቅ በቃል መደባደብን ከመረጥን ቀይ መብራት እያበራን ነው፡፡ ሌሊት ተነስቶ ማስቀደስን ከተውን፣ ለራሳችን ልዩ ጊዜ ካጣን፣ ከንስሃ አባቶቻችን ጋር የመገናኘት ፍላጎታችን ከሞተብን ነፍሳችን ባትሪ እየጨረሰች እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ወርቃማ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ህይወት ትኩር ብሎ መመልከት ካቃተን፣ ስዕሉ ከህሊናችን ከጠፋ ይህ በመሆኑም ምንም ካልመሰለን ወደ ራሳችን ማየት እንዳለብን ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ሁሌ ትችትና ንቀት የተሞላ ሃሳብ ከልባችን ከወጣ ልባችን ታውቃለህ፣ ትበልጣለህ፣ ሌሎች ግን አይረቡም፣ አያውቁም፣ አልተረዱም ካለን battery low እያለን ነው፡፡የዓሳ አጥማጁን የጴጥሮስን የዋህ ልብ ጥለን የመጽሐፍት ሸምዳጁን የቀያፋን ልብ በውስጣችን ካገኘን አደጋ ላይ ነን፡፡ መቅረዙ የተወሰደበት መብራቱ የጠፋበት ሰው ሆኖ መኖር ምቾት ይሰጣል? በሞተ ህሊና በደነዘዘ ልብ መመላለስ ያስደስታል? የድንኳናችን/ሰውነታችን/ መብራት ጠፍቶ እስከመቼ ይኖራል?
እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅክ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ስራህን አድርግ፡፡አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ፡፡ ራዕ 2፤5
Friday, January 10, 2014
ሰላም
ለሁላችሁ፤- አንድ የህክምና ዶክተር በባህር ዳርቻ ንፋስ ሲቀበል ባህሩ ላይ የሚዋኙ ዳክዬዎች ትንሽ እንደዋኙ ፍግም ብለው እንደሚሞቱ
ተመለከተ፡፡ ሁኔታውን ሲያጠና የዳክዬ በሽታ እንደያዛቸው ተረዳ፡፡ ሄዶም በቤተ ሙከራ ለወፎቹ መድሃኒት ፈለሰፈ፡ መድሃኒቱን ይዞ መጥቶ ሊሰጣቸው ሲሞክር ዳክዬዎቹ ሊቀርቡት አልቻሉም፡፡ ሲጠራቸው
እየፈሩ ይሸሹ እና ይሞቱ ነበር፡፡ አይኑ እያየ ዳክዬዎቹ አለቁ፡፡ ዶክተሩም እነዚህ ዳክዬዎች ወደ እኔ መቅረብ የፈሩት አኔ አነሱን
ስላልመሰልኩ ነው እኔ ዳክዬ ብሆን ኖሮ ቀርቤ አክማቸው ነበር አለ፡፡ አምላክ ለምን ሰው ሆነ ትላላችሁ? የሚሉ ሰው መሆኑም ክበሩን
እንደማይመጥን የሚገምቱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አምነንበት አንድንድን በመድሃኒቱም፣ እንድንፈወስ፣እኛነታችንን የሚረዳ ጌታ
በሥጋ ተገልጧል፡፡ሰው መሆኑን የትትናውን እና የፍቅሩን ውሳኔ ማመን ያጸድቃል፡፡ ጥንት በሙሴ ዘመን በሲና ተራራ በእሳት ተገልጦ
ድምጹን ልንሰማ አንችልም እንሞታለን ብለን ፈርተን ሸሽተን ነበር፡፡ዛሬ ግን እኛን መስሎ በሥጋ ስለተዛመድን የልባችን አምላክ እና
እውነተኛ አባት አድርገነዋል፡፡
እባካችሁ
ለሌሎች ሼር አድርጉት
Monday, October 21, 2013
ሰላም ለሁላችሁ፤- አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው፡፡ ያዕ 1፤26 አንደበት የሰማይንም የምድርንም ፍጥረታት የሚያስቆጣ ክፉ ነገር የሚወጣት በር ነው፡
ሰላም
ለሁላችሁ፤- አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው፡፡ ያዕ
1፤26 አንደበት የሰማይንም የምድርንም ፍጥረታት የሚያስቆጣ ክፉ ነገር የሚወጣት በር ነው፡፡ ነገር ግን መዝጊያ ተበጅቶለታል፡፡
ያም እግዚአብሔርን የሚፈራ አእምሮ ነው፡፡ ደግሞም እሳት የሚተፋ እስካሁን ዘመን ድረስ ሳይጠፋ ያለ ደራጎን ነው፡፡ ዓለምን ማቃጠል
የሚችል እሳት ይወጣበታል፡፡ እንዲሁም መልካም ህሊና ላለውም ሰው የሞቱ ልቦች የሚነቃቁበት መንፈሳዊ ሙቀት የሚወጣበት ቅዱስ እሳት
መፍሰሻ ነው፡፡ በጌታም ዘንድ የምንዳኝበት መረጃ ነው፡፡ በፍርድ
ቀን ለምንናገረው ለእያንዳንዱ ነገር መልስ ትሰጣላችሁ ብሎናል ጌታችነ
ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ስለዚህ እንደፈለገ የሚንሸራተት አንደበታችንን ዝም አንበለው፡፡ ለጌታ ክብር ፣ ለሃይማኖት ወ.ዘ.ተ. ብለህ ነውና አንደበትህ ቢረክስ ችግር የለውም የሚለንን የዲያቢሎስን ማባበል
በስሙ ልንገስጸው ይገባል፡፡የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሰራም ተብሎ ተጽፏልና፡፡ያዕ 1፤20
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት
Tuesday, October 8, 2013
ሰላም ለሁላችሁ፤- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከውጭ ከማባከን የመጣውን ልጅ ተቀብሎ ወደ ቤቱ እንዳስገባው እንደጠፋው ልጅ አባት ነው፡፡
ሰላም
ለሁላችሁ፤- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከውጭ ከማባከን የመጣውን ልጅ ተቀብሎ ወደ ቤቱ እንዳስገባው እንደጠፋው ልጅ አባት ነው፡፡
ያለምክንያት በምህረቱ ተቃባይ ነው፡፡ አንዳንዴ ቸርነቱ ለፍርድና ለሙግት ሰዎች አነጋጋሪ ነው፡፡ ምህረት ግን ከፍርድ በፊት እና
በላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከፍርዱ ቀን በፊት የፍቅሩና የማዳኑ ቀን
የቀደመው፡፡ ደግሞም ከቤቱ በግፍ ለሚወገዱ ሰዎች ከበር ቆሞ ከተስፋ መቁረጥና ወድቆ ከመቅረት የሚጠብቅ ነው፡፡ አይነስውሩ ሰው
ጌታዬ አበራኝ ባለ ጊዜ ከምኩራብ ቢያስወጡትም ከበር ቆሞ ጠብቆታል፡፡ ልጆቹ ከእርሱ አይን ፊት ስላሉ በየትኛውም ሁኔታ በቂ ዋስትና
አላቸው፡፡ ሉቃ 15;24 ዮሐ 9;35
እባካችሁ
ለሌሎች ሼር አድርጉት visit www.ashenafigmariam.blogspot.com
Monday, September 23, 2013
ሰላም ለሁላችሁ፤- እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በአያትህ በሎይድ በእናትህ በኤውንቄ ነበረባቸው 2ኛ ጢሞ 1;5 ግብዝነት ያለበት እምነት የሚሰራው በሰው ፊት ነው፡፡ ማመኑ ለሰዎች ጥቅም ከመሆን ይልቅ የሰውን ህሊና ማናደጃ፣ የተደበቀ አለማዊነት በውስጡ የሚሰራ ነው፡፡
ሰላም
ለሁላችሁ፤- እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በአያትህ በሎይድ በእናትህ በኤውንቄ ነበረባቸው 2ኛ ጢሞ 1;5 ግብዝነት ያለበት እምነት የሚሰራው በሰው ፊት ነው፡፡ ማመኑ ለሰዎች ጥቅም
ከመሆን ይልቅ የሰውን ህሊና ማናደጃ፣ የተደበቀ አለማዊነት በውስጡ የሚሰራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዘመናችን እኔ የማርያም ነኝ ወይ
እኔ የኢየሱስ ነኝ የሚሉ ፉከራዎችን የምናገኘው ግብዝነት ጓዙን ጠቅልሎ ስለገባብን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እኔ የአጵሎስ ነኝ
እኔ ኬፋ እኔ የጳውሎስ እኔ የክርስቶስ ነኝ ያሉ ግብዞችን ከዚህ ስንፍናቸው እንዲላቀቁ መከረ፡፡1ኛ ቆሮ 1፤12 የክርስቶስ፣ የጳውሎስ፣ የኬፋ፣ የአጵሎስ፣ የማርያም ድንግል መሆን ባልከፋ
እምነቱ ግን በእግዚአብሔር ፊት ባለዋጋ ከመሆን ይልቅ ግልጽ ድንጋዩን ጥለን ያነሳነው ሌላ መንፈሳዊ ጦር መሳርያ/ስውር ድንጋይ/
ሆኖ እምነት መልኩን እንዲያጣ ጣዕሙን እንዲቀይር የመንፈሳዊነት መዓዛ እንዲጠፋ አድርጓል፡፡ አንዳንድ አማኖች የእግዚአብሔር ሰው
ከመሆን ይልቅ ኦርቶዶክሶች ናቸው እንዲባሉ ላይ ላዩን ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡አኒህ ሰዎች ጾማቸውን በሰው ፊት ያደረጉትን የዋሆች
ይመስላሉ፡፡ደግሞ ሌሎቹ የኢየሱስ ተቆርቋሪ ሆነው በክፉ ትዕቢታቸው ኢየሱስን የሚያጠቁሩ አሉ፡፡እነሎይድ ግን ግብዝነት በሌለበት
እምነት ተመሰገኑ እምነታቸው አይመካም እዩኝ እዩኝ አይልም እንደነኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ፊት የሆነ እና በመንፈስ ቅዱስ የተመሰከረለት
ነው፡፡ሉቃ 1;6
እባካችሁ
ለሌሎች ሼር አድርጉት
Monday, September 2, 2013
ሰላም ለሁላችሁ፤- አንጥረኛው ወርቁን በእሳት የምታቃጥለው እስከ መቼ ነው ቢሉት ፊቴን እሳካይበት ነው አላቸው፡፡ ጌታችን እንደእሳት በሆነ መንገድና መከራ የሚያሳልፈን የራሱን መልክ ማለትም ቅድስናን፣ ትዕግስት፣ ለሰው መኖርን፣ ደግነትን፣ ጠንካራ ስብዕናን እንድንለብስ ነው
ሰላም
ለሁላችሁ፤- አንጥረኛው ወርቁን በእሳት የምታቃጥለው እስከ መቼ ነው ቢሉት ፊቴን እሳካይበት ነው አላቸው፡፡ ጌታችን እንደእሳት በሆነ መንገድና መከራ የሚያሳልፈን የራሱን መልክ ማለትም
ቅድስናን፣ ትዕግስት፣ ለሰው መኖርን፣ ደግነትን፣ ጠንካራ ስብዕናን እንድንለብስ ነው፡፡ በሚቆረቁር መንገድ ያስሮጠናል ግን ወፍራም
ጫማ በእግራችን ላይ ያስርልናል፡፡ ሞልቃቃና ቅምጥል ገጽ እንዲኖረን አይሻም፡፡ ኩራት የሚናገሩ ከንፈሮች በእሳቱ እንዲቀደሱ ይሻል፡፡ኢሳ6;7
በእርሱ ላይ መመካታችን እንኳ ራስን ዝቅ በማድረግ ቸርነቱን በማግነን
እንዲሆን ይሻል፡፡1ኛ ጴጥ 2;16 አብረውን የሚኖሩ በእኛ እንዲያርፉ አብረውን የሚውሉ ከልባችን በሚወጣው ሃሳብ እንዲሳቡ ትከሻችን
የተወደደውን አምላክ መሸከሙን ዓለም እንዲመለከት በእሳት እንሰራለን፡፡ እግዚአብሔርን ገና አላወቅነውም በየቀኑ በትምህርት በይበልጥ
ደግሞ በሕይወት ትግል ውስጥ እያየነው እንመጣለን ያን ጊዜ እግዚአብሔርን አይቼዋለሁ እና ሰውነቴ ድና ቀረች /ጵንኤል/ እንላለን:: www.ashenafigmariam.blogspot.com
ይጎብኙት
እባካችሁ
ለሌሎች ሼር ያድርጉት
Subscribe to:
Posts (Atom)