Wednesday, April 30, 2014

የምትወዱአቸውን ግደሏቸው

የምትወዱአቸውን ግደሏቸው ጌታ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ልባችንን አስፍቶ ነው፡፡ እንውደድ ካልን ብዙ ሰዎችን እንወዳለን፡፡ የሰውን ህይወት ከሚገዙ ሁለት ነገሮች አንዱ ፍቅር ነው፡፡ ህግም እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ሃይልህም በፍጹም ሃሳብህ ውደድ እና ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ በሚሉ ሁለት ትዕዛዞች ተጠቅልሏል፡፡ሉቃ 10፤27 ስለዚህ የሰው ነፍስ በሁለት ፍቅሮች መካከል ትኖራለች፡፡ እግዚአብሔርን የምንወድበት ፍቅር በፍጹም ነፍስ፣ ሃይል፣ ልብ እና ሃሳብ ነው፡፡ ይሄ ፍቅር በተፈቃሪው/በጌታ/ ላይ ይታመናል ተስፋ ያደርጋል ምንጊዜም የማይጥል እንደሆነ አስቦ ይደገፍበታል፡፡ከራስ በላይ ይወዳል ምናልባት ምቾትን ጥሎም ቢሆን ቅር አይለውም፡፡ ጌታም እንዲህ ከወደዱት አይጥልም፡፡ ፍቅሩም ለዘላለም ነው፡፡ አለኝ ቢሉት ይኖራል እርሱ ያውቃል ቢሉት ያውቃል፡፡ ቢወራረዱበት ይረታል፡፡ እወቁልኝ ቢሉት አያሳፍርም፡፡ ሰውን ግን በዚህ አይነት መንገድ መውደድ ጉዳት ያመጣል፡፡ ያልታዘዘም መንገድ ነው፡፡ ሰው የሚወደደው እንደራስ ነው፡፡ ለሰው የምታደርጉትን ነገር ከራሳችሁ አንጻር እስቲ እዩት፡፡ ትንሽ ልጅ ተርቦ ብታዩ በልባቸችሁ የኔ ልጅ ቢሆንስ ስትሉ የበለጠ ትራራላችሁ፡፡ የሰው ኃጢያት ተገልጦ በአደባባይ ሲዋረድ ብታዩ እኔ ብሆንስ ስትሉ እጅግ ታዝናላችሁ፡፡እኔ እንደምሞት እርሱም እኮ እንዲሁ ነው ትላላችሁ፡፡ እንደራስ መውደድ እንዲህ ነው፡፡ አንዳንድ ግዜ ግን ሰው ሰውን በፍጹም ነፍስ በፍጹም ልብ በፍጹም ሃሳብ በፍጹም ሃይል መውደድ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ተስፋ መመኪያ ያደርገዋል፡፡የማይሳሳት ፍጹም አድርጎ ያስበዋል፡፡ ስህተቱን በሚያዩ ሰዎች ላይ ቂም ይይዛል፡፡ ያለእርሱ መኖር አልችልም ብሎ ያብዳል፡፡ የሞተ እንደሆነ ገመድ አቀብሉኝ እንዴት እኖራለሁ ወይ አብሬ እቀበራለሁ ተውኝ ብሎ ለያዥ ያስቸግራል፡፡ እርሱ ከተቀየመ ሰማይ የተደፋበት ያክል ተስፋ ቢስ ይሆናል፡፡ አንድም ቀን ይሞታል ብሎ አያስብም፡፡ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ጋር አመሳስሎ የማይወድቅ ትምክት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡እርሱ ካለኝ ምን ሆናለሁ ይላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ከሚጸልይባቸው ደቂቃዎች ይልቅ ለዚህ ሰው ችግሩን የሚነግርባቸው ሰዓቶች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ቤቱን በሰው አጥንት ግድግዳውን በሰው ሥጋ ያጠረ ሰውን ይመስላል፡፡አቤት ይሄ ሰው ውድቀቱ! ይህ ሰው ልቡ የተሰበረ እለት ለመጠገን በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ትምክህቱን ሲነጠቅ መኖሩም አብሮ ይጠፋል፡፡ እርሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ሳለ ራሱን እንደ ማይጠቅም አድርጎ ይቆጥራል ለከፍተኛ የስነልቦና ችግር ይጋለጣል፡፡ እባካችሁ የምትወዷቸውን ሰዎች በአእምሮአችሁ ግደሏቸው፡፡ አናቴ ብትሞት? አባቴ ቢሞትስ ?ፍቅረኛዬ ወይ ሚስቴ ወይ ባለቤቴ ቢሞትስ ? ልጄ ቢሞትስ? ያ ችግር ሲገጥመኝ እየተሯሯጠ የሚያግዘኝ ባለስልጣን ወዳጄ ቢሞትስ? እኔ ካለሁ አይዞህ ያለኝ አጎቴ ድንገት ቢያንቀላፋስ……. መኖር እችላለሁ? በሉ እስቲ! ጌታ ለተከታዮች እንደሚሞትና በሶስተኛው ቀን እንደሚነሳ ይነግራቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን አላስተዋሉም፡፡ ሁሌ መኖር ያለ ይመስላቸው ነበር፡፡ማር 9፤9 ጌታችን አስቀድሞ በወዳጆቹ አእምሮ ሞቱን አትሞ ነበር፡፡ የምትወደዱ ሰዎችም አንድ ቀን እንደማትኖሩ ለሚወዷችሁ ንገሩ፡፤ ዝም ብላችሁ አትኑሩ፡፡ ለህጻናት ልጆቻችሁ እንኳ እኔ አንድ ቀን እሞታለሁ የማይሞተው አምላክ አሳዳሪ በሰማይ አለላችሁ እንዳትፈሩ በሏቸው፡፡ አለሁ እያላችሁ እንዳታልሏቸው፡፡ የአብ ጸጋ የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቃችሁ