Monday, October 21, 2013

ሰላም ለሁላችሁ፤- አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው፡፡ ያዕ 1፤26 አንደበት የሰማይንም የምድርንም ፍጥረታት የሚያስቆጣ ክፉ ነገር የሚወጣት በር ነው፡



ሰላም ለሁላችሁ፤- አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው፡፡ ያዕ 1፤26 አንደበት የሰማይንም የምድርንም ፍጥረታት የሚያስቆጣ ክፉ ነገር የሚወጣት በር ነው፡፡ ነገር ግን መዝጊያ ተበጅቶለታል፡፡ ያም እግዚአብሔርን የሚፈራ አእምሮ ነው፡፡ ደግሞም እሳት የሚተፋ እስካሁን ዘመን ድረስ ሳይጠፋ ያለ ደራጎን ነው፡፡ ዓለምን ማቃጠል የሚችል እሳት ይወጣበታል፡፡ እንዲሁም መልካም ህሊና ላለውም ሰው የሞቱ ልቦች የሚነቃቁበት መንፈሳዊ ሙቀት የሚወጣበት ቅዱስ እሳት መፍሰሻ ነው፡፡ በጌታም ዘንድ የምንዳኝበት  መረጃ ነው፡፡ በፍርድ ቀን ለምንናገረው ለእያንዳንዱ ነገር መልስ  ትሰጣላችሁ ብሎናል ጌታችነ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ስለዚህ እንደፈለገ የሚንሸራተት አንደበታችንን ዝም አንበለው፡፡ ለጌታ ክብር ፣ ለሃይማኖት ወ.ዘ.ተ.   ብለህ ነውና አንደበትህ ቢረክስ ችግር የለውም የሚለንን የዲያቢሎስን ማባበል በስሙ ልንገስጸው ይገባል፡፡የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሰራም ተብሎ ተጽፏልና፡፡ያዕ 1፤20
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

Saturday, October 19, 2013

አይናማ ፍቅር_ ክፍል አንድ/በቀሲስ አሸናፊ/ www.ashenafigmariam.blogspot.com ይሄ ፍቅር ስሜትን ኮርኳሪ ሆኖ በሃይል ሊጀምር ይችላል አንዳንዴ ይከሰታል ሳይባል በመላመድ ሊጀምር ይችላል፡፡ ንጥቅ የሚያደርግ፣ ደስታ የሚፈጥር፣ በተለይ ለልብ እረፍት የሚሰጥ ሆኖ ይሰማል፡፡ይህ ፍቅር ብዙ ጊዜ በጊዜው ይጀምራል፡፡ ሰውየው ራሱን ለኑሮ ባዘጋጀ ጊዜ ተረጋግቶ ይከሰታል

አይናማ ፍቅር_ ክፍል አንድ/በቀሲስ አሸናፊ/ www.ashenafigmariam.blogspot.com

       ይሄ ፍቅር ስሜትን ኮርኳሪ ሆኖ በሃይል ሊጀምር ይችላል አንዳንዴ ይከሰታል ሳይባል በመላመድ ሊጀምር ይችላል፡፡ ንጥቅ የሚያደርግ፣ ደስታ የሚፈጥር፣ በተለይ ለልብ እረፍት የሚሰጥ ሆኖ ይሰማል፡፡ይህ ፍቅር ብዙ ጊዜ በጊዜው ይጀምራል፡፡ ሰውየው ራሱን ለኑሮ ባዘጋጀ ጊዜ ተረጋግቶ ይከሰታል፡፡ ሲግልም እንደሸክላ ምጣድ ነው፡፡ ቀስ ብሎ ይጀምራል እየቆየ ሲመጣ እየጋለ ይመጣል፡፡ መብረጃ የሚባል ጊዜ ገደብ የለውም፡፡ አብርሃምና ሣራ በዚህ ፍቅር ውስጥ ነበሩ፡፡ ካረጁ ከሸመገሉ በኋላ ተቃቅፈው ይተኙ ነበረ፡፡ዕብ 11፤12  ልጅ የወለዱትም በዚሁ ፍቅር ውስጥ ሆነው ካረጁ በኋላ ነበር፡፡ ይሄ ፍቅር ከውጫዊው ደም ግባት ብቻ አይነሳም ውስጥን በጥልቀት የማየት ድፍረት አለው፡፡ የሚያየውም ቀምሶ ለመትፋት አይደለም፡፡ ያፈቀረውን የሚሸከምበት መላ ለማበጀት ነው እንጂ! በእርሱ ዘንድ መልክ ደም ግባት ቦታ የላቸውም እያልኩ አይደለም ዋናው መለኪያው ግን የውስጥ ማራኪነት ነው፡፡ በዚህ ፍቅር የተያዙ ሰዎች የሚደንቅ ስብዕና አላቸው፡፡ ሁሌ ይፍለቀለቃሉ፡፡ ወቀሳ ማብዛትና በራስ የመተማመን ችግር የለባቸውም፡፡ ፍቅረኛቸው የትም ብትሄድ የትም ቢሰራ ቅናት የተባለ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ ይልቁንም ለሩቁ ሰዋቸው መልካም እየለመኑ ይታገሳሉ እንጂ፡፡  ፍቅር አይቀናምና፡፡1ኛቆሮ13;4
       የአይናማው ፍቅር ሌላው ጠባይ ሁኔታዎች አይቀያይሩትም፡፡ ሣራ እና አብርሃም በረሃቡ ዘመን ወደ ጌራራ ንጉስ በተሰደዱና ንጉሱ ሳራን ሊያገባት በተዘጋጀ ጊዜ ንጉስ አግብታ ንግስት ከመሆን ከድሃው ባሏ ከአብርሃም ጋር ድህነትን መረጠች፡፡ዘፍ12;19  ፍቅሩ በዘመን፣ በሁኔታዎች፣ የተፈተነና ያለፈ ነው፡፡ በደህናም ጊዜ አፍቃሪ በችግርም ጊዜ አፍቃሪ፣ በረሃብም ዘመን አፍቃሪ በጥጋብ ጊዜ፣ ልጅ ሳይወልዱም አፍቃሪ ልጅ ወልዶም፣ ከስታም ጠቁራም አፍቃሪ ከስሮም ተጎሳቁሎም አፍቃሪ ነው፡፡ይህ ፍቅር እንደ አዋሽ ውሃ ቀስ እያለ ይሞላል፡፡ ሲፈስ ድምጹ አይሰማም/ጭቅጭቅ አይሰማበትም/ በጥልቀት ረዥም ርቀት ይሄዳል፡፡ ለውሳኔ አይቸኩልም ለመለያየትም ለመጋባትም ግራ ቀኙን ያያል፡፡በዚህ ፍቅር የተያዙ ሰዎች እንጀራ ይበላላቸዋል እንቅልፍም ይተኛሉ፡፡ ፍቅሩ ጤነኛ በመሆኑ ጉዳት የሚባለውን ፉርጎ ከኋላ አያስከትልም፡፡ ጸሎታቸውም ጌታ ሆይ ፍቃድህ ከሆነ ይሁን ካልሆነም ያንተ ፍቃድ ይሁን የሚል ነው፡፡ማቴ 26፤42 ካንቺ ከተለየሁ ሞት እመርጣለሁ ያላንተ መኖር አልችልም የሚሉ የሞኝ መዝሙሮችን አይዘምርም፡፡ እግዚአብሔር ያለ እርሷ መኖር አለብህ ካለው ሳያጉረመርም ፍቃዱን ይቀበላል፡፡ እርሷም እንዲሁ!
        ይሄ የተረጋጋ ፍቅር ወደ ትዳር ለመጓዝ የተሰናዳ ሰረገላን ይመስላል፡፡ ስሜታዊነትን አጥብቆ ይሸሻል፡፡ ከእውነተኛው የህይወት ገጽታ ዘወር ማለት አይችልም፡፡ አይን ስላለው በደንብ ያያል፡፡ ሐዋርያው /ጳውሎስ ስለዚህ ፍቅር የጻፈውን ተመልከቱ፡፡ 1 ቆሮ13 4-8
1- ይታገሳል፤- ጓደኛውን ሲያጠና ደካማ ጎኗን ተመልክቶ ትዕግስትን ይለምድበታል፡፡እሷም እንዲሁ፡፡ አትንኩኝ ስህተት አልመልከት አይልም፡፡ እርሱ ሰው ነውና እንደርሱ ሥጋ የለበሰችውን ጓደኛውን እንደ መልዓክ ቆጥሮ ስትሳሳት ተዓምር እንደተፈጠረ ግርግር አይፈጥርም፡፡ ይልቁንም ትዕስተኛ ይሆናል፡፡ ትከሻውን እያሰፋ አብሮ ኖርን ይመርጣል፡፡ የእርሷ ጉድለት በእርሱ እንደሚሞላ ይገነዘባል፡፡
2- ቸርነት ያደርጋል፤- ፍቅሩን ሲሰጥ ከልቡ ነው/በቸርነት/ ከገንዘቡ ሲያካፍላት ሂሳብ እየሰራ አይደለም በቸርነት ነው፣ ያደረገውን ሁሉ እስኪረሳ ድረስ ቸር ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሰው ይሄን ቢያደርግ እንደሞኝ የተቆጠረ እየመሰለው ጠባቡን መንገድ ትቶ በሰፊው ንፍገት መጓዝ ይወዳል፡፡ ፍቅር የቸርነትን መንገድ ስለሚያሳየው ሚስቱ ብትሆንም ባትሆንም ከመርዳት ወደ ኋላ አይልም፡፡
3- አይቀናም፡፡ ቅናት ራስን አብዝቶ ከመውደድ የሚመጣ ህመም ነው፡፡ ሁሉን ለኔ የሚል አመለካከት ውጤት ነው ፡፡ ስለምታፈቅረው የምትቀና የሚመስላት ሴት ተሳስታለች፡፡ እራሷን በጣም ስለምታፈቅር ነው እንጂ! ቅናት በራስ ያለመተማመንም ችግር ነው፣ ታማኝ ያልሆነም ሰው መገለጫ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደርሱ የሚሰርቅ ስለሚመስለው የሚቀና አለ፡፡ፍቅር ግን በራሱ እርገጠኛ ስለሆነና ስለማያጎድል አይቀናም፡፡
4- አይመካም፤- የወደደችኝ ገንዘብ ስላለኝ ነው የት ትሄዳለች; በግድ አብራኝ ትኖራለች፣ የወደደኝ ሁሉ የሚማረክበት ውበት ስላለኝ ነው ተገዶ አብሮኝ ይቀመጣል .. በፍቅር ውስጥ አይደመጡም፡፡ እነዚህ ለጊዜው የሚለመልሙ ስትመለሱ ግን የማታገኝዋቸው ስር አልባ ዛፎች ናቸው፡፡ ፍቅር ሜዳ ላይ ይወዳል ምንአልባትም ምንም ምክንያት ላይፈልግ ይችላል፡፡ እንዲሁ ወደደን እንደተባለ! ዮሓ 316 ይሄ ልብ መመካት አይችልም ማፍቀር እንጂ!
5- አይታበይም፤- ከኔ ጋር ሆነሽ ሰው መሰልሽ አማረብሽ፣ እርሷም እኔን አግኝተህ ጫማ ቀየርክ፣ በኔ ባለ ግሪን ካርድ ሆንክ በማለት በትዕቢት አይገዳደሩም፡፡ እግዚአብሄርን ተስፋ የሚያደርግ ፍቅር ሁልጊዜ ትሁት ነው፡፡1 ጰጥ 3 5
6- የማይገባውን አያደርግም፤- ትክክል በሆነ መንገድ ይሄዳል፡፡ ፍቅረኛን ለማብሸቅ ክፉ አይናገርም አያስፈራራም፣ያስቆጣትን ለማናደድ ከማትወደው ሰው ጋር ለመታየት አትሞክርም፣ በችግር ቀን ድምጹን አያጠፋም፣ ቤተሰብን የሚጎዳ ተግዳሮት አያመጣም፣ ክብረ ነክ ልምምዶችን/ስድብን ጉልበትን/ አይወድም፣ ከክብር አሳንሶ አይንሽ ላፈር አይልም፣ የወለደውን ልጅ አይክድም፡፡ ሁሌ ቀጥተኛ እና ቅን መንገድንይከተላል፡፡
7- ራሱን አይፈልግም፤- ይሄ ፍቅር እንደቀይ ሽንኩርት ነው፡፡ ተልጦ ተልጦ ለራሱ ምንም ልብስ አይተርፈውም ወይም እንደ ጌታ ራቁቱን እስኪቀር ያለውን ይሰጣል፡፡ አግብቻት ከገንዘቧ ተካፍዬ! አግብቼው የሃብቱ ተካፋይ ከሆንኩ እርሱ ገደል ይግባ አይልም፡፡ እርሱ ፍቅር እንጂ ቁሳቁስን አያገባም፡፡
8- አይበሳጭም፤- በሆነው ባልሆነው ነገር ተነካሁ ብሎ አይበሳጭም፡፡ ሁሌ እንክብካቤ ፈላጊ አይደለም፡፡ ተንከባካቢውም  እንክብካቤ እንደሚፈልግ ማወቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ተካፍሎ አዳሪ ነው ይሰጣል ይቀበላል፡፡ብስጭቱን በአደባባይ ሰው ይይልኝ ብሎ አያወጣም፡፡ ረጋ ብሎ ራሱን አብርዶ ወደ መፍትሄው ይመለሳል፡፡ ኮስታራ ባህልና ወግ በፍቅር ታጋሽ ላለመሆን ምክንያት እንዲሆን አይፈቅድም፡፡
 1 ቆሮ 135-8
1-በደልን አይቆጥርም፤- የወደደ ልብ በደልን ቶሎ ይቅር ይላል፡፡ ተጣልተው እንኳ ጀምበር አትጠልቅም፡፡ ያጠፋችውን ነገር ስትጠይቁት ዘርዝሮ መናገር ያቅተዋል፡፡ እርሷም እንዲሁ፡፡ ሰው እንዲህ አድርጎኝ እንዲህ አድርጎኝ የሚለው ፍቅሩ እየላላ ሲመጣ ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ በደልን መቁጠር የለም፡፡
2- ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል ከአመጽ ጋር አይደሰትም፤- አይናማ ፍቅር ዋሽቶ ካሳመነ በኃላ ደስ አይለውም፣ ሚስጢሩን ደብቆ ጓደኛ አይሆንም፣ አታሎ አይጎዳም፣ ከአንገት በላይ እወድሻለሁ እወድሃለሁ ተባብሎ አይሸነጋገልም፣ እውነተኛ እና ንጹህ ነው፡፡ ግልጽ እና እውነተኛ በመሆኑ እንደተጎዳ አይቆጥርም፡፡
3- ሁሉን ይታገሳል፤- በችግርም ጊዜ በደስታም ጊዜ በስህተትም ጊዜ በድካምም ጊዜ በቁጣም ጊዜ በንዴትም ጊዜ እንደሳራ በረሃቡም ጊዜ እንደኑሃሚን በስደቱም ጊዜ ይታገሳል
4-ሁሉን ያምናል፤- እንዲህ ሲባል ጅል ነው ማለት አይደለም ፡፡ መታመን የሚገባቸው ጉዳዮችን ለማመን የሚቸግራቸው ተጠራጣሪ አፍቃሪዎች ብዙ አሉ፡፡ ይሄ ፍቅር ግን ተጠራጣሪ አይደለም ከጀርባ ሌላ ታሪክ ስለሌለው አማኝ ነው፡፡የዋህነቱ ሁሉን እንዲያምን ያደርገዋል በኑሮውም ደስተኛ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን የማያምኑ ሰዎች ልበ ጠንካራዎች ናቸው በቀላሉ ለፍቅር ለመሸነፍ ይቸግራቸዋል፡፡ ይሄ ፍቅር አማኝ ቢሆንም ክፉ ደጉን ግን ማወቅ ይችላል፡፡
5-በሁሉ ይጸናል፤- ብዙ አፍቃሪዎች በአንድ መርጋት ይቸግራቸዋል፡፡ ሁሌ የተሻለ ሲፈልጉ የተሻለውን ሊያጡት ይችላሉ፡፡ በፍቅራቸው ጽናትን ያጡ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ይሄ ፍቅር ባለው ነገር ይጸናል፡፡ ፍቅሩ በቤተሰብ፣በማጣት፣ በወሬ፣ በስሜታዊነት በተፈተነ ጊዜም ጽኑ ሆኖ ይቆማል፡፡
6-ለዘወትር አይወድቅም፡- ይሄ ልዩ ባህሪው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ፍቅራችን ቀዘቀዘ ብለው ይደናገጣሉ፡፡ የድሮው ፍቅር ጠፍቶብናል ብለው ሌላ ፍለጋ ወደ ውጭ ለመሄድ ይጀምራሉ፡፡ ይሄ እንዴት ያለ ስህተት ነው! አይናማ ፍቅር አይወድቅም ምን አልባት ይዳፈን ይሆናል፡፡ የተዳፈነ እሳት እንዳለ ይቀመጥና ጫር አድርገው እንጨት ሲያጋድሙበት መቀጣጠል ይጀምራል፡፡ ቤቱ ይሞቃል ምግቡም ይበስላል፡፡ ፍቅርም እንዲሁ ነው መቆስቆስ ይፈልጋል የሁለቱን መፈላለግና መቀራረብ መደናነቅና መተያየት ይፈልጋል፡፡ እንደገና ታድሶ ህያው ይሆናል፡፡ እንደ አብርሃምና ሳራ በሽምግልናም ይግላል፡፡ ከያዘ አይለቅም! ይሄ ነው የአይናማ ፍቅር መገለጫውይቆየን