Monday, September 23, 2013

ሰላም ለሁላችሁ፤- እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በአያትህ በሎይድ በእናትህ በኤውንቄ ነበረባቸው 2ኛ ጢሞ 1;5 ግብዝነት ያለበት እምነት የሚሰራው በሰው ፊት ነው፡፡ ማመኑ ለሰዎች ጥቅም ከመሆን ይልቅ የሰውን ህሊና ማናደጃ፣ የተደበቀ አለማዊነት በውስጡ የሚሰራ ነው፡፡



ሰላም ለሁላችሁ፤- እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በአያትህ በሎይድ በእናትህ በኤውንቄ ነበረባቸው 2ኛ ጢሞ 1;5   ግብዝነት ያለበት እምነት የሚሰራው በሰው ፊት ነው፡፡ ማመኑ ለሰዎች ጥቅም ከመሆን ይልቅ የሰውን ህሊና ማናደጃ፣ የተደበቀ አለማዊነት በውስጡ የሚሰራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዘመናችን እኔ የማርያም ነኝ ወይ እኔ የኢየሱስ ነኝ የሚሉ ፉከራዎችን የምናገኘው ግብዝነት ጓዙን ጠቅልሎ ስለገባብን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እኔ የአጵሎስ ነኝ እኔ ኬፋ እኔ የጳውሎስ እኔ የክርስቶስ ነኝ ያሉ ግብዞችን ከዚህ ስንፍናቸው እንዲላቀቁ መከረ፡፡1ኛ ቆሮ 1፤12  የክርስቶስ፣ የጳውሎስ፣ የኬፋ፣ የአጵሎስ፣ የማርያም ድንግል መሆን ባልከፋ እምነቱ ግን በእግዚአብሔር ፊት ባለዋጋ ከመሆን ይልቅ ግልጽ ድንጋዩን ጥለን ያነሳነው ሌላ መንፈሳዊ ጦር መሳርያ/ስውር ድንጋይ/ ሆኖ እምነት መልኩን እንዲያጣ ጣዕሙን እንዲቀይር የመንፈሳዊነት መዓዛ እንዲጠፋ አድርጓል፡፡ አንዳንድ አማኖች የእግዚአብሔር ሰው ከመሆን ይልቅ ኦርቶዶክሶች ናቸው እንዲባሉ ላይ ላዩን ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡አኒህ ሰዎች ጾማቸውን በሰው ፊት ያደረጉትን የዋሆች ይመስላሉ፡፡ደግሞ ሌሎቹ የኢየሱስ ተቆርቋሪ ሆነው በክፉ ትዕቢታቸው ኢየሱስን የሚያጠቁሩ አሉ፡፡እነሎይድ ግን ግብዝነት በሌለበት እምነት ተመሰገኑ እምነታቸው አይመካም እዩኝ እዩኝ አይልም እንደነኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ፊት የሆነ እና በመንፈስ ቅዱስ የተመሰከረለት ነው፡፡ሉቃ 1;6
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

Saturday, September 7, 2013

አይናማ ፍቅር_ ክፍል አንድ/በቀሲስ አሸናፊ/ ይሄ ፍቅር ስሜትን ኮርኳሪ ሆኖ በሃይል ሊጀምር ይችላል አንዳንዴ ይከሰታል ሳይባል በመላመድ ሊጀምር ይችላል፡፡፡፡

አይናማ ፍቅር_ ክፍል አንድ/በቀሲስ አሸናፊ/
ይሄ ፍቅር ስሜትን ኮርኳሪ ሆኖ በሃይል ሊጀምር ይችላል አንዳንዴ ይከሰታል ሳይባል በመላመድ ሊጀምር ይችላል፡፡፡፡ ንጥቅ የሚያደርግ፣ ደስታ የሚፈጥር፣ በተለይ ለልብ እረፍት የሚሰጥ ሆኖ ይሰማል፡፡ይህ ፍቅር ብዙ ጊዜ በጊዜው ይጀምራል፡፡ ሰውየው ራሱን ለኑሮ ባዘጋጀ ጊዜ ተረጋግቶ ይከሰታል፡፡ ሲግልም እንደሸክላ ምጣድ ነው፡፡ ቀስ ብሎ ይጀምራል እየቆየ ሲመጣ እየሞቀ ይመጣል፡፡ መብረጃ የሚባልጊዜ ገደብ የለውም፡፡ አብርሃምና ሣራ በዚህ ፍቅር ውስጥ ነበሩ፡፡ ካረጁ ከሸመገሉ በኋላ ተቃቅፈው ይተኙ ነበረ፡፡ ልጅንም የወለዱትም በዚሁ ፍቅር ውስጥ ካረጁ በኋላ ነበር፡፡ ይሄ ፍቅር ከውጫዊው ደም ግባት ብቻ አይነሳም ውስጥን በጥልቀት የማየት ድፍረት አለው፡፡ የሚያየውም ቀምሶ ለመትፋት አይደለም፡፡ ያፈቀረውን የሚሸከምበት መላ ለማበጀት ነው እንጂ! በእርሱ ዘንድ መልክ ደም ግባት ቦታ የላቸውም እያልኩ አይደለም ዋናው መለኪያው ግን የውስጥ ማራኪነት ነው፡፡ በዚህ ፍቅር የተያዙ ሰዎች የሚደንቅ ስብዕና አላቸው፡፡ ሁሌ ይፍለቀለቃሉ፡፡ ወቀሳ ማብዛትና በራስ የመተማመን ችግር የለባቸውም፡፡ ፍቅረኛቸው የትም ብትሄድ የትም ቢሰራ ቅናት የተባለ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ ይልቁንም ለሩቁ ሰዋቸው መልካም እየለመኑ ይታገሳሉ እንጂ፡፡ ሐዋርያው ፍቅር አይቀናም እንዳለ፡፡1 ቆሮ 13;4
የአይናማው ፍቅር ሌላው ጠባይ ሁኔታዎች አይቀያይሩትም፡፡ ሣራ ከአብርሃም ጋራ በረሃቡ ዘመን ወደ ጌራራ ንጉስ በተሰደዱና ንጉሱ ሊያገባት በተዘጋጀ ጊዜ ንጉስ አግብታ ንግስት ከመሆን ከድሃው ባሏ ከአብርሃም ጋር ድህነትን መረጠች፡፡ዘፍ12;19 ፍቅሩ በዘመን፣ በሁኔታዎች፣ የተፈተነና ያለፈ ነው፡፡ በደህናም ጊዜ አፍቃሪ በችግርም ጊዜ አፍቃሪ፣ በረሃብም ዘመን በጥጋብ ጊዜ አፍቃሪ፣ ልጅ ሳይወልዱም አፍቃሪ ልጅ ወልዶም፣ ከስታም ጠቁራም አፍቃሪ ከስሮም ተጎሳቁሎም አፍቃሪ ነው፡፡ይህ ፍቅር እንደ አዋሽ ውሃ ቀስ እያለ ይሞላል፡፡ ሲፈስ ድምጹ አይሰማም/ጭቅጭቅ አይሰማበትም/ በጥልቀት ረዥም ርቀት ይሄዳል፡፡ ለውሳኔ አይቸኩልም ለመለያየትም ለመጋባትም ግራ ቀኙን ያያል፡፡በዚህ ፍቅር የተያዙ ሰዎች እንጀራም ይበላላቸዋል እንቅልፍም ይተኛላቸዋል፡፡ ፍቅሩ ጤነኛ በመሆኑ ጉዳት የሚባለውን ፉርጎ አያስከትልም፡፡ጸሎታቸውም ጌታ ሆይ ፍቃድህ ከሆነ ይሁን ካልሆነም ያንተ ፍቃድ ይሁን የሚል ነው፡፡ ካንቺ ከተለየሁ ሞት እመርጣለሁ ያላንተ መኖር አልችልም የሚሉ የሞኝ መዝሙሮችን አይዘምርም፡፡ እግዚአብሄር ያለእርሷ መኖር አለብህ ካለው ሳያጉረመርም ፍቃዱን ይቀበላል፡፡ እርሷም እንዲሁ! …..ይቆየን!
ሼር አድርጉት