Thursday, August 29, 2013

ሰላም ለሁላችሁ፤- ቅ/ጴጥሮስ በደብረታቦር የጌታውን ብርሃን ሲመለከት ድፍት ብሎ ወደቀ፣ማቴ 17;6 ቅ/ዮሐንስ በራዕይ ጌታ ኢየሱስን በሰባቱ መቅረዞች መሃል ሲመለከተው እንደሞተ ሰው ሆኖ ወደቀ፡



ሰላም ለሁላችሁ፤- ቅ/ጴጥሮስ በደብረታቦር የጌታውን ብርሃን ሲመለከት ድፍት ብሎ ወደቀ፣ማቴ 17;6 ቅ/ዮሐንስ በራዕይ ጌታ ኢየሱስን በሰባቱ መቅረዞች መሃል ሲመለከተው እንደሞተ ሰው ሆኖ ወደቀ፡፡ራዕ 1;17 ሁለቱም ግን ተመልሰው ተነስተው የእግዚአብሔርን ሀሳብ  አገልግለዋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መሆን እየወደቁ እየተነሱ ነው፡፡ልጅ በአባቱ ፊት የሚያድገው እየወደቀ እየተነሳ ነውና፡፡ ማንም ሰው በጌታው ፊት እንኳ ሆኖ በራሱ ጸንቶ አይቆምም፡፡ የራሱ ጉልበት፣የራሱ ጽድቅ፣ ማስተዋሉ ይከዳዋል፡፡ ነገር ግን ከፊቱ የቆመው አባት እንደ ቅ/ጴጥሮስ እጁን ዘርግቶ ከመስጠም ያድነዋል እንጂ! እንደገና ያቆመዋል እንጂ! ስለዚህ በፊቱም ሆኜ ራሴን ማስተካከል ስላልቻልኩ ወደ ዓለሜ ብመለስ ይሻላል ብላችሁ የሞኝ ውሳኔ እንዳትወስኑ፡፡ ጌታችሁ ራሱን ያስተካከለውን አልጠራም ይልቁንም እናንተ ደካሞች ሸክም የከበደባችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ አለን እንጂ፡፡ ማቴ 11፤28
 እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት

Tuesday, August 27, 2013

ሰባኪ ክፍል ሁለት



ሰባኪ ክፍል ሁለት
ጥንካሬ -ሰባኪ በሁሉም መንገድ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ በአገልግሎቱ የበዛ ከንቱ ውዳሴ ይፈስልታል፡፡ እርሱን በትህትና ሲቋቋም ከንቱ ክስ ይደርስበታል፡፡ ሰይጣን ይህን የሚያደርገው ስለራሱ እያወራ ራሱን ሲከላከል በትዕቢት እንዲያዝ ነው፡፡ በእነዚህ በሁለቱም ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ደግሞም ከዓለም የሚመጣው ክብርና ገንዘብ ሃሳቡን ወደ ሌላ ሊመልስበት ስለሚችል በዛም ብርቱ መሆን አለበት፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር ስለሆነ የቤት ኪራይ ሃምሳ ብር አይሆንለትም ኑሮውን እንደ አለሙ በጋራ የሚጋፈጠው ነው፡፡ማን ኛውም ሰው የሚደርስበትን መከራ ሰው እንደመሆኑ ተካፋይ ነው፡፡ ወለጋ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰባኪ በዓለም ላይ እናቱ ብቻ ነበሩ ዘመዱ፡፡ በየለቅሶው ቤት እየሄደ ለሃዘንተኞች የመጽናናት ትምህርት ይሰጣል፡፡ አንድ ቀን ግን እርሱ ለአገልግሎት ወደ ወረዳ በሄደበት እናቱ ሞተዋል ተብሎ ተጠራ፡፡ራሱን ሊቆጣጠር አልቻለም፡፡ በአስተማረው ህዝብ ፊት ትዝብት ውስጥ እስኪወድቅ አዘነ፡፡ ከተረጋጋ በኋላ ምነው ቢሉት፡ እግዚአብሔርን በጣም ስለምወደው በእኔ ላይ ሃዘን የሚያመጣ አልመሰለኝም ነበር፡፡ እናቴንም አብዝቼ ስለምወዳት የምትሞት አልመሰለኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ ምንም ስሙን ባገለግል ሰው መሆኔን፣ የሰው ሁሉ ፈተናና ትግል የሚጠብቀኝ መሆኔን ተቀንያብሁ አለ፡፡
ንባብ ፤- የሚያነበው የሌለው ሰባኪ የሚሰብከው የለውም፡፡ ዓለማዊ ዕውቀት በየቀኑ እንደሚሻሻል ሁሉ መንፈሳዊም ዕውቀት ማደግ አለበት፡፡ ምዕመናን አንዳንድ ጊዜ በራሳቸው ጥረት ብዙ ወደ ላይ እያደጉ ይሆናል ሰባኪው ከእነሱ አንሶ መታየት የለበትም፡፡ ዘመናዊውም ዓለም ወደ ፊት በሄደ ቁጥር የአማኞች ስነልቦና በዛው መጠን ይሰቀላል፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ይህን ሚዛን ጠብቆ ሁሉን የሚረታ አገልግሎት እንዲኖረው ሕይወቱንና መጽሐፍትን አብዝቶ ማንበብ ይኖርበታል፡፡ ዋናው መግቦቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት ካልሆነ የልብ ወለድ ሃሳብና  ለአሮጊቶች ተረት አገልጋይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች ቅዱሳት/አዋልድ/ መጽሐፍትን ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ጋዜጦችን መጽሔቶችን ሚዲያዎችን በጥንቃቄ ማየት አለበት፡፡ በስነ ልቦና በጾታና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሐፍት መንፈሳዊ ከሆኑት ጋር መነበብ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በአብዛኛው ዶግማ ነክ ጽሑፎችን መጻፍ ይቀናቸዋል ፡፡የግብጽ አባቶች ደግሞ መንፈሳዊነት ላይ በጥልቀት ይጽፋሉ፡፡ እነዚህንም ማንበብ ለዛ ያለው ሰባኪ ለመሆን ይረዳል፡፡ ለእውቀት እና ለግንዛቤ የሌላ እምነት ተከታዮችን ጽሁፎች ማንበብ ቢኖረበት ማንነቱን እንዳይቀሙት መጠንቀቅ አለበት፡፡ በተለይ የፕሮቴስታንት ጽሁፎች ማንነትን የማጣጣል መንፈሳዊው ባህል ላይ የመቀለድ ጸባይ ስላለባቸው የሰባኪው ስነልቦና ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ማንነት ከጠፋ በኋላ ልመልሰው ቢሉት ብዙ ጉዳት ካላመጣ እሺ አይልም፡፡ 
ስሜት - ሰባኪ ሰው ነው፡፡ የትኛውም ሰው የሚሰማው ደስታ፣ ሃዘን፣ ድብርት፣ ብቸኝነት፣ ራሰን መጥላት፣ መሰልቸት፣ ተስፋ መቁረጥ የመሳሰለው ስሜት ይፈራረቅበታል፡፡ ይህ ስሜት በአገልግሎቱ እንዳይገለጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ተስፋ ቆርጦ ከሆነ  ሰው እኮ ዋጋ የለውም ብሎ ቢያስተምር የእግዚአብሔርን ሃሳብ ይቃወማል፡፡እርሱ ቆጡ ከሆነ ጌታ ቀሳፊ ነው ሊለን አይገባም፡፡ ሁልጊዜ ከራስ ስሜት ተነስቶ ማስተማር፣ መምከር፣ ድምዳሜ ላይ መድረስ ብዙ ጉዳት ያስከትላል፡፡አዲስ አበባ ውስጥ አንድ አገልጋይ አውቃለሁ በጣም ስሜታዊ ነው፡፡ ሁል ጊዜ ሽብር መስበክ ይወዳል፡፡ችግር  ሊፈጠር ነው፣ ጉድ ሊፈላ ነው፣ እሳት ሊነድ ነው ወዘተ……ማለት ይወዳል፡፡ ለመስበክም ለመዘመርም ይሞክራልና ሲሰብክ መርዶ ነጋሪ ይመስላል፡፡ ምዕመናን ተጠንቀቁ እንዲህ ሊሆን  ቀርቧል!  አዲስ አበባ ልትበጠበጥ ነው! ጸልዩ! የመሳሰሉ አስደንጋጭ ሃሳብ ወለድ ቃላትን ይናገራል፡፡ምእመናንም ይሄ ምንድነው; ሃገር ሰላም አይደለም እንዴ; ብለው እስኪጠይቁ ድረስ ያሸብራቸዋል፡፡ ነገር ግን የተበጠበጠው የራሱ ስሜትና ሃሳብ ነበር፡፡ ይሄ ጎጂ ስሜታዊነት ነው፡፡ ሰባኪው መጥፎ ስሜት ሲሰማው ዝም ማለት አለበት፡፡የራሱን ፍርሃት ለሰው ማጋባት የለበትም፡፡
በረከት - የአገልጋይ መጋቢው አሳዳሪው እግዚአብሔር ነው፡፡ በኪዳኑ ነው የሚያኖረው፡፡ ከልቡ ካገለገለ ዋጋውን ይረሳበት ዘንድ እግዚአብሔር አመጸኛ አይደለም፡፡
                                 ማን ቀረ በሜዳ ማን ቀረ በዱር
                                 አንተን ብሎ ወጥቶ እግዚአብሔር  እንዳለ ገጣሚው
     በየአጥቢያው የሚከፈለው ደሞዝ ትንሽ ጉርሻ ነው እንጂ ዋናው ደሞዝ በሥላሴ እጅ ነው ፡፡ ሙሉ ትኩረቱን የእግዚአብሔርን ቤት ለመስራት ካዋለው ጌታ የራሱን ቤት አሳምሮ ይሰራለታል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ አገልጋዩ በጌታ ሰገነት ላይ የራሱን ቤት የመስራት ዓለማ ብቻ ይዞ ሲደክም ይታይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዳሰበው ሊደላደልለት አይችልም፡፡ መልካሙን አሳዳሪ አምኖ ምንም ሳይቀረው ልፍት ማለት አለበት፡፡ አምላክ በገንዘብ፣ በቤት፣ በልጆች፣ በትዳር፣ አብዝቶ ይባርካል፡፡ ባለ  ብዙ ወዳጅም ያደርጋል፡፡ ዓላማን ትቶ የራስን ቤት ለመስራት መድከም ግን ምናልባት ሙዳይ ምጽዋት ሰባሪ ወይ በሙስና ሥራ ተሳታፊ፣ አታላይ ሰው አድርጎ ሊያበላሽ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ ሰራተኞች በከንቱ ይደክማሉተብሎ ተጽፏል፡፡
ሌላ ዓለም -በልቡ መናኝና ጎበዝ አገልጋይ የሆነ አንድ ወዳጅ ነበረኝ ለጌታው ሲለፋ አቅም አይቀርለትም፡፡ አንድ ቀን እባክህ ሰይጣን ሌላ ዓለም እያሳያኝ ነው፡፡ ድካምህ ምንድ ነው እከሌ ዓለምን እያገለገለ ተመችቶት ይኖር የለወይ ይለኛል አለኝ፡፡ በእርግጥ ለአገልጋይ ጌታ ብቻ ነው ዓለሙ! ሮጦ ያተረፈው በልቡ መቀነት የቋጠረው የወርቅ ገንዘቡ ብዙ የሚገዛበት ውድ መክሊቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሌላ ዓለም ቢኖር እንኳ የውርደቱ ስፍራ እንጂ የክብሩ አይሆንም፡፡ ጴጥሮስ ጌታን ትቶ እሳት ሲሞቅ መዋረድ የጀመረው በገረዶች ነበረ፡፡ ሰው ማጥመዱን ትቶ ወደ አሳ አስጋሪነቱ በተመለሰም ጊዜ ልፋትና ባዶ መረብ ብቻ ነበር የተረፈው፡፡ዮሐ 21፤3 አገልጋይ ሌላ ዓለም ፈልጎ ቢንሸራተት መዋረድ የሚጀምረው የተናቁ ባላቸው ተራ መንገዶች ነው፡፡ ጎደለብህ ወደ ፊት ምን ትሆናለህ ዛሬ ካልተማርክ ካልነገድክ የት ትወድቃለህ; እያለ ጠላት የዓለምን መንጠልጠያዎች ከጌታ ክንድ አስበልጦ ያሳየዋል፡፡ የባልንጀሮቹን ቤት፣ ዓለምን ያገለገሉ እኩዮቹን ኑሮ እያሳየ ልቡን ይዋጋዋል፡፡እንደ ጌታችን ወደ ታላቅ ተራራ በምኞት ወስዶ ያቆመዋል፤ ወድቀህ ብትሰግድልኝ/ አገልግሎትህን ብትተውልኝ/ ይህን ዓለም እሰጥሃለሁ ይለዋል፡፡ማቴ 4፤9 ያልበረታ ከሆነ ሞቶ ይቀራል፡፡አገልጋይ ራሱን ከሌላ ዓለም ውጊያ በጸሎትና በትጋት ሊጠብቅ ይገባል፡፡
 
ትጋት፡-  የእግዚአብሔርን ስራ በቸልታ የሚሰራ የተረገመ ይሁን ይላል መጽሐፍ! በጸሎት ብዙ መትጋት፣ በመስበክ በመዘመር ብዙ መትጋት፣ በማንበብ በምመከር ብዙ መትጋት፣ በመሞከር በመሞከር ብዙ መትጋት፣ ቤተክርስቲያንን በማልማት ብዙ መትጋት፣ የካህናቱን ኑሮ ለመቀየር ብዙ መትጋት፣ በሰላሙም በጦርነቱም ሰዓት መትጋት ያስፈልጋል፡፡በተነቀፉም ሰዓት ፍጥነትን ሳይቀንሱ ብዙ መትጋት፣ በተመሰገኑም ሰዓት ውዳሴን ለማዳመጥ ቆም ሳይሉ ብዙ መትጋት ይገባዋል፡፡
ማዳመጥ ፡- የማገልገል ዕድል ማግኘት ብዙ ማወቅ አይደለም፡፡ የሚያስተምራቸውን ሰዎች በደንብ ማዳመጥ ችግሮቻቸውን  ለይቶ ለማወቅ ይረዳዋል፡፡ ከብርታታቸውም ለመማር ያግዛል፡፡ በደንብ ያዳመጠ ሰው በሚገባ ሊደመጥ ይችላል፡፡ ቶሎ ቶሎ መናገር ያለመማር ወይ ያለመብሰል ምልክት ነው፡፡ ሰነፍ እንኳ ቢሆን ዝም ያለ እንደ አዋቂ ይቆጠራል ፡፡
ያለስስት፡-  አንዳንድ ሊቃውንት ቆሎ ትምህርት ቤት ውሻ ነክሶኝ የተማርኩትን በቀላሉ አልሰጥም የሚል ስስት ይታይባቸዋል፡፡ አገልጋይ ግን የዛሬ እንጂ የነገ ሰው አይደለምና በሰጠው እድሜ ያለውን፣ የሚያውቀውን ያለስስት ማስተማር አለበት፡፡እንደ ልባሙ መጋቢ በተሾመበት ገንዘብ ያለስስት አበዳሪ መሆን ይገባዋል፡፡ አንድ ወንድም በታክሲ እየሄደ የሚያነበውን ስልክ ደውሎ ሲያካፍል ሰምቼአለሁ፡፡ ያወቁትን  ለማሳወቅ መቸኮል እንዴት ደስ ይላል፡፡ ፍቅር እንደቀይ ሽንኩርት ናት ዝም ብላ እየሰጠች ታልቃለች ፡፡አገልጋይ ጉልበቱን ዕውቀቱን ሳይሰስት ለጌታው ክብር ማዋል አለበት፡፡ብዙ ሰዎች ስላልመጡ ብሎ ከእውቀቱ ቆጥቦ ቢያስተምር ብዙዎች ሲሰበሰቡለት የሚያውቀውን ሁሉ ካልሰበኩ ቢል የእግዚአብሔርን ሃሳብ ከማገልገል እንደወጣ ሊረዳ ይገባዋል፡፡
ዝግጅት፡-  ምንም የሚያስተምረውን እንደሚያውቀው ቢሰማውም ወይ የሚዘምረውን እንደለመደው ቢያስብ መዘጋጀት ግን አለበት፡፡ ቤታችን ውስጥ ተከድኖ የዋለ ያልሞቀ ምግብ የምንመገበው ሲቸግረን ብቻ ነው ካልሆነ እሳት ላይ አሙቀን እንመገበዋለን፡፡  አገልጋዩም አገልግሎቱን እሳት ማስነካት አለበት፡፡ በመሰዊያው ፊት የሚቀርበው አገልግሎት የቀዘቀዘ ሙት መሆን የለበትም፡፡ በዝግጅት የታሸ እና የጣፈጠ እንዲሆን መጣር አለበት፡፡  ዘማሪው በሄደበት አገልግሎት ሰባኪው ካስተማረው ትምህርት ጋር የሚሄድ መዝሙር ለመዘመር መዘጋጀት አለበት፡፡ ክርስቶስ ከሞት ተነሳ ብሎ አስተምሮ ዘማሪው የማይሞተው ሞተ ብሎ ማሳረግ የለበትም፡፡በእለቱ ለሚነረው አገልግሎት ትንሽ ሰዓት መንበርከክ የዝግጅቱ ዋናው አካል ነው፡፡
ጥልን ልዩነትን መጸየፍ ፡- ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አንዳንድ ሰባኪዎች ጥልን በሃይማኖት ስም በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ መስበክ እንደትልቅ አገልግሎት ይቆጥሩታል፡፡ ይሄን በማድረጋቸው ትንሽም አይሰማቸውም፡፡ ቤተክርስቲያን ቅድስና አልባ እንደትሆን ትልቅ በር የሚከፍትው አንዱ ይሄ መንገድ ነው፡፡ በመቅደሱ የጥፋት ርኩሰት ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል ከተባለው አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሰባኪ ጥልን መጸየፍ አለበት!! 
    ከእግዚአብሔር ይልቅ በከበቧቸው አድናቂዎቻቸው ሚመኩ ሰዎች ለጥል ቅርብ ናቸው፡፡አጋዥ አለን እያሉ በእግዚአብሔር ከማመን ዘወር የሚሉ፣ ወይ ለጠባቸው የምዕመናንን ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች አልፎ አልፎ ይታያሉ የሚሰማቸውን ይናገራሉ የሚያመጣውን ውጤት ምን ይሁን ምን ግድ የላቸውም፡፡ በክርስቶስ አውደ ምህረት ጥልን ማገልገል እጅግ አሳፋሪ ታሪክ ነው፡፡ ጠብን በህዝብ ፊት አውጆ የወረደ አገልጋይ አገልጋይ ሆኖ ባይጠራ ይሻለው ነበር፡፡ ጥልን መጸየፍ የጌታን መስቀል መሸከም ነው፡፡በመስቀሉ ሰላም አውርዶ ከመምጣት በቀር ሌላ አገለግሎት ከኛ ይራቅ!  በፍጹም ሰው እንዲለያይ ማድረግ ተገቢ አይደለም! በወንድሞች መሃል ልዩነትን የሚዘራ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተጠላ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በተለይ በአንድ አንድ መነኮሳት ዘንድ/ሕዝቡን አጋጭተው ከሃገር በሚወጡ/፣ በባህታውያን ዘንድ፣ በአፍቃሪ ማህበራት ዘንድ፣ ትልቅ ሰባኪ ነን ዘማሪ ነን በሚሉ ዘንድ፣ ከእኔ በቀር ሃይማኖተኛ በሚሉት ትምህርት አልባ ሰዎች ዘንድ ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያንን መዓዛ ያጠፋል፡፡ ይቀጥላል ሼር አድርጉት

Friday, August 23, 2013



ሰላም ለሁላችሁ፤- ሙሴ በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፡፡ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ ታመነ ነው፡፡ዕብ 3፤5 እግዚአብሔርን እንደ ባርያ ከህጉና ከቅጣቱ ተነስቶ መፍራት አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ልጅ ከምህረቱ እና ከተወደደ አባትነቱ ተነስቶ መፍራት ግን እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም ህጉ ፍጹም ካልሆኑ አይምርም፡፡ ህጉ አሰሪ ነው ያልሰራውን አይከፍለውም ይከሰዋል እንጂ፡፡ ከዚህ የተነሳ ሰው በደከመ ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ከእግዚአብሔር ፊት እንደቃየል ሊኮበልል ይችላል፡፡ ትህትናውም ፍርሃቱም ቅጣትን ብቻ ፈርቶ ይሆንና በአምላኩ መኖር አሰልቺ ሥራ ይሆንበታል፡፡ምህረቱን ያመነ ግን ሁል ጊዜ በፍቅሩ ይደገፋል፡፡ ምህረቱ ለዘለዓለም ነውና በዚህ እምነት ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የለም፡፡ መዝ 135፤1 እንደ ልጅም በቤቱ /በቤተክርስቲያን/ የሚኖር የአባቱን ቤት እንደራሱ ቤት ይመለከታል፡፡ስለቤቱ ሥነስርዓት አስተማሪ አይፈልግም፡፡ ስለ ቤተሰቦቹም ክብር ሌላ ባዕድ አስረጂ አይፈልግም፡፡ ስለወላጆቹ አጠራር እና ቁልምጫ ፍቅሩ እንጂ በር ላይ የሚለጠፍ ማሳሰቢያ አያስረዳውም፡፡እንደ ልጅ አምኖ መኖር የአማኙን ነፍስ ሰላማዊ ያደርጋታል፡፡ ያደላድላታል፡፡
 እባክዎ ለሌሎች      ሼር ያድርጉት

Tuesday, August 6, 2013

ሰላም ለሁላችሁ

ሰላም ለሁላችሁ፤- ይህ የእመቤታችን መታሰቢያ ጾም ሁላችንም በፍቅር የምንጾመው ብዙ በረከትም የተቀበልንበት ነው፡፡ ማርያም ድንግል ጌታችንን ለመውለድ ፍቃደኛ በመሆኗ እና ከእርሱም ጋር እስከ ስቅለቱ አሳዛኝ የመከራ ጊዜ በማሳለፏ በስሟም በተቀበልነው ድንቅ በረከት ከልባችን እንወዳታለን፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን ብለን በምንጸልየው ጸሎት ብዙ መልስ እንዳገኘን ሁሉ በእነዚህም ሳምንታት በጸሎቷ እና እምነታችንን በሚያውቀው ልጇ ዘንድ እንደምንሰማ አንጠራጠርም፡፡ውሃው ወይን እንዲሆን ጋኖቹ መታጠብ ነበረባቸው፡፡ እኛም እንዲሁ ነን፡ ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ሁሉ ወደ ንስሃ አባት ሄደን ተናዘን በጌታም ፊት በተሰበረ መንፈስ ልንቆም፣ ሥጋውን ልንበላ ደሙን ልንጠጣ ይገባል፡፡ የጸሎት ርዕስ ይዘን ልንጾም ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ስላሉ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልንጸልይ ይገባል፡፡ በሶርያ ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎችም ወንድሞች በጦርነት እየተፈጁ ነው፡፡ በግብጽም ክርስቶሳውያን አደጋ ላይ ናቸው፡፡ ለምንወዳት ሃገራችንም፣ ለወንጌል መስፋፋት፣ ርኩሰት የተሞላችውን ይህችን ዓለም ለተቀላቀሉ ሕጻናት ከጥፋት እንዲድኑ፣ አባቶቻችን ፍርድ ጽድቅ እንዳይለያቸው፣ መሪዎቻችን ህዝባቸውን እና ሃገራቸውን እንዲወዱ፣ መንፈስ ቅዱስ በልባችን እንዲሰራ ከልባችን ልንጸልይ ይገባል፡፡….የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ ታላቅ ሃይል ታደርጋለችና፡፡ያቆ 5:16 ቅድስት ሆይ ለምኝልን
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት


ሰላም ለሁላችሁ፤- ይህ የእመቤታችን መታሰቢያ ጾም ሁላችንም በፍቅር የምንጾመው ብዙ በረከትም የተቀበልንበት ነው፡፡ ማርያም ድንግል ጌታችንን ለመውለድ ፍቃደኛ በመሆኗ እና ከእርሱም ጋር እስከ ስቅለቱ አሳዛኝ የመከራ ጊዜ በማሳለፏ በስሟም በተቀበልነው ድንቅ በረከት ከልባችን እንወዳታለን፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን ብለን በምንጸልየው ጸሎት ብዙ መልስ እንዳገኘን ሁሉ በእነዚህም ሳምንታት በጸሎቷ እና እምነታችንን በሚያውቀው ልጇ ዘንድ እንደምንሰማ አንጠራጠርም፡፡ውሃው ወይን እንዲሆን ጋኖቹ መታጠብ ነበረባቸው፡፡ እኛም እንዲሁ ነን፡ ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ሁሉ ወደ ንስሃ አባት ሄደን ተናዘን በጌታም ፊት በተሰበረ መንፈስ ልንቆም፣ ሥጋውን ልንበላ ደሙን ልንጠጣ ይገባል፡፡ የጸሎት ርዕስ ይዘን ልንጾም ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ስላሉ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልንጸልይ ይገባል፡፡ በሶርያ ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎችም ወንድሞች በጦርነት እየተፈጁ ነው፡፡ በግብጽም ክርስቶሳውያን አደጋ ላይ ናቸው፡፡ ለምንወዳት ሃገራችንም፣ ለወንጌል መስፋፋት፣ ርኩሰት የተሞላችውን ይህችን ዓለም ለተቀላቀሉ ሕጻናት ከጥፋት እንዲድኑ፣ አባቶቻችን ፍርድ ጽድቅ እንዳይለያቸው፣ መሪዎቻችን ህዝባቸውን እና ሃገራቸውን እንዲወዱ፣ መንፈስ ቅዱስ በልባችን እንዲሰራ ከልባችን ልንጸልይ ይገባል፡፡….የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ ታላቅ ሃይል ታደርጋለችና፡፡ያቆ 5:16 ቅድስት ሆይ ለምኝልን
እባካችሁ ለሌሎች ሼር አድርጉት